ሞቼና ቦራጎ ዋሻ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ዳሞታ ተራራ ስር የሚገኝ እጅግ አስገራሚ ዋሻ ነው፡፡
ዋሻው ከሶዶ ከተማ በሆሳና - አዲስ አበባ በኩል ከዋናው መንገድ በስተቀኝ በኩል በ 12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ሞቼና ቦራጎ ዋሻ ከባህር ወለል በላይ በ 2 ሺህ 340 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
የዋሻው ጣሪያ 33 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን 50 ሜትር ስፋት አለው፡፡
በዓለም የበረዶ ዘመን ተብሎ በሚጠራው አስቸጋሪ ዘመን የሰው ልጅ ሕይወትን የታዳገ ዋሻ እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል።
ከፈረንሳይ እና ከጀርመን በመጡ አርኪኦሎጂስቶች በተደረገው ጥናት መሠረት በዓለም የበረዶ ዘመን ወቅት የሰው ልጅ በዋሻው የተንሰራራበት ስፍራ እንደሆነም ይገለፃል።
የዋሻው ግድግዳ ተፈጥሯዊ በሆኑ ዓለቶች የተገነባ ሲሆን ከአሜሪካ፣ ከፈረንሣይ እና ከጀርመን በመጡ አርኪኦሎጂስቶች በተካሄደው የአርኪኦሎጂ ቁፋሮ የሰው ልጅ በዋሻው ውስጥ ከ 58 ሺህ እስከ 70 ሺህ ዓመታት በፊት ይኖር እንደነበር ያሳያል ተብሏል፡፡
ሞቼና ቦራጎ ዋሻ 500 ሰው አንደላቆ ማኖር የሚችል ሰፊ ዋሻ ነው።
በተደረጉ ጥናቶች ቦቼና ቦራጎ ዋሻ የሰው ልጆች በዓለም የበረዶ ዘመን ወቅት ተጠልለው ያሳለፉበትና የተሳካ ፍልሰት ከተከናወነባቸው የዓለም 7 ቦታዎች መካከልም አንዱ ነው።
የሰው ልጅ የተረጋጋ ኑሮ የጀመረበት፣ ምግብ አብስሎ የተመገበበት፣ ልብስ ሸምኖ የለበሰበት ጥንታዊ ስፍራ ሲሆን፤ ለዚህም መገለጫ የሆኑ የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች በዋሻው ይገኛሉ።
በጥናት የተገኙ ቁሳቁሶችም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን የተረከቡ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በትዕግስቱ ቡቼ