ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ ናት፡- ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ

2 Mons Ago 355
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ ናት፡- ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ገልጸዋል።
 
ፕሬዚዳንቱ በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ስብሰባ ላይ ተካፍለዋል።
 
ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ በአህጉሪቱ ለተገኙ እመርታዎች እውቅና በመስጠት የአፍሪካ ህብረትን አቅም ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ ወሳኝ ተግዳሮቶች እንደሚቀሩ መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
 
ፕሬዚዳንቱ አምስት ቁልፍ ነጥቦች ያሏቸውን በንግግራቸው አንስተዋል።
 
በዚህም አካታችነትን ማረጋገጥ፣ የገንዘብ ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳዎችን ማስቀደምና ማስተካከል፣ ጠንካራ የንግግር ባሕልን ማዳበር እና በዓለም አቀፍ መድረክም የኅብረቱን ትስስርና ውህደት ማሳደግ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦች መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።
 
ለተፈፃሚነቱም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዚዳንት ታየ አረጋግጠዋል።
 
በአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ የስብሰባ መድረኩ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ እና የሃገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
 
በስብሰባው የሚነሱ ሀሳቦችን በማካተት በቀጣይ በየካቲት ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ምክረ ሀሳብ እንደሚነሳ ይጠበቃል።
 
በሙሉ ግርማይ
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top