ጎግል ፕሌይ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል ጀመረ

1 Mon Ago 290
ጎግል ፕሌይ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል ጀመረ

የጎግል ፕሌይ (Google Play) አልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል ጀምሯል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት፤ የጎግል ፕሌይ የአልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል መጀመሩ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ተጽእኖ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህ ምዕራፍ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ባለቤቶች መተግበሪያዎቻቸውን በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ ዲጂታል መድረኮች ላይ እንዲያትሙ አዲስ እድሎችን እንደሚከፍትም ገልፀዋል።

መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት በርካታ ተነሳሽነቶችን በመተግበር እየሰራ መሆኑን ገልጸው ይህ አዲስ ጅማሮ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ነው ብለዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ይህንን እድል ተጠቅመው ችግር ፈቺ መተግበርያዎችን በማልማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚኒስቴሩ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ለኢትዮጵያውያን ስታርታፖች  ምቹ ሥነ-ምህዳርን ለማዳበር ከሚተገበሩ ሰራዎች መካከል በአለም አቀፍ የዲጂታል መድረኮች  እንዲሳተፉ የሚያስችሉ አለማቀፋዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ እድሉን ለማመቻቸት የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

እያይዘውም ይህ አዲስ እድል ኢትዮጵያውያን ገንቢዎች የጎግል ፕሌይን አለምአቀፍ ታዳሚዎች በቀጥታ በማግኘት መተግበሪያዎቻቸው ሰፊ እይታን እንዲያገኝ እና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችላል ማለታቸውን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የሀገር ውስጥ ገንቢዎች ከአካባቢው፣ ከማህበረሰቡ ወግና አኗኗር ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን መተግበሪያዎች በማልማት እንዲሁም ለአለማቀፍ ገበያው የሚመጥን ስራ እንዲሰሩ እንደሚበረታቱም ገልፀዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top