የካንሰር ታማሚ የነበሩ እናቷን ችግር ለመቅረፍ አዲስ ፈጠራ የሰራችው ወጣት ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸነፈች

30 Days Ago 355
የካንሰር ታማሚ የነበሩ እናቷን ችግር ለመቅረፍ አዲስ ፈጠራ የሰራችው ወጣት ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸነፈች

 

የካንሰር ታማሚ የነበሩ እናቷን ችግር ለመቅረፍ አዲስ ፈጠራ ያስተዋወቀችው ወጣት ከታዋቂው ጀምስ ዳይሰን ድርጅት ዓለም አቀፍ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡

ወጣቷ የካንሰር ህመምተኞች በኬሞቴራፒ ህክምና ወቅት የሚያጋጥማቸውን የፀጉር መነቀል ለመከላከል የሚረዳ አዲስ ቴክኖሎጂ በመስራቷ ነው ዓለም አቀፍ የፈጠራ ውድድሩን ማሸነፍ የቻለችው፡፡

የ24 ዓመቷ ወጣት ተማራማሪዋ ኦሊቪያ ሁምፍሬስ እናቷ የካንሰር አምጪ ህዋሶች በሰውነታቸው ውስጥ እንዳይባዙ ሲወስዱት የነበረው የኬሞቴራፒ ህክምና በፀጉራቸው ላይ ያስከተለውን ጉዳት ለማስቀረት ወደዚህ የፈጠራ ስራ መግባቷን ገልጻለች፡፡

ወጣቷ ህልሟና ጥረቷ ተሳክቶ የኬሞቴራፒ ህክምና የሚያደርጉ የካንሰር ህመምተኞች ፀጉር እንዳይነቀል መከላከል የሚያስችል “በጭንቅላት ላይ የሚገጠም የማቀዝቀዥ መሳሪያ” መፍጠር ችላለች፡፡

አዲሱ መሳሪያ የኬሞቴራፒ ህክምና ለሚያካሄዱ የካንሰር በሽተኞች ምቹ እንደሆነና  ህመምተኞች መሳሪያውን በተመጣጣኝ ክፍያ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡

ፈጠራውን የሰራችው ወጣት ጀምስ ዳይሰን ተብሎ የሚጠራ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ሽልማት በህክምና ዘርፍ ማሸነፍ ችላለች፡፡

በህክምናው ዘርፍ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘለቂ መፍትሄ ለሚሆኑ የፈጠራ ስራዎች እውቅና የሚሰጠው ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ብቁ ተማሪዎችን እያወዳደረ ከ400 በላይ ወጣት የፈጠራ ስራ ለሰሩ ኢንጂነሮችና ሳይንቲስቶች ድጋፍ አድርጓል፡፡

አዲሱ ግኝት የካንሰር ታማሚዎች ኬሞቴራፒ በሚያደርጉበት ወቅት የሚያገጥማቸውን የፀጉር መነቀል በማስወገድ ትልቅ ልዩነት ሊፈጥር እንደሚችልም ዘገባው አመላክቷል፡፡

ወጣቷ የሰራችው የፈጠራ ስራ ከመላው ዓለም ከ29 ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ከቀረቧቸው 2ሺህ የፈጠራ ስራዎች መካከል የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ዘ ኢንድፔንደንት ዘግቧል፡፡

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top