የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል: - ዶክተር መቅደስ ዳባ

6 Hrs Ago 31
የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል: - ዶክተር መቅደስ ዳባ
የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀናጀ ስራ ማከናወን እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስገነዘቡ።
 
የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር እየተከናወነ ያለውን ስራ በሚመለከት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩም የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
 
የጤና ሚኒስትሯ በበየነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሚኒስቴሩ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
 
ወረርሽኙን ለመግታት እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
 
በተለይም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በእቅድ መስራት፣ የቅኝትና የቁጥጥር ስራን ማጠናከር፣ በቤት ለቤት ስራ ማህበረሰቡን በማንቃትና በማደራጀት አካባቢን እንዲያጸዱ ለማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
 
ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ እና ለወባ መራባት ምቹ የሆኑ ረግረጋማ አካባቢዎችን የማዳፈን ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
 
ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሕብረተሰቡን በተደራጀ መልኩ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በማድረግ የመከላከል ሚናውን እንዲወጣ ነው ያሳሰቡት።
 
በኢትዮጵያ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ማዕከል ያደረገ የወባ በሽታን የመቆጣጠር ስራ ላይ ያለውን መልካም ተሞክሮ ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።
 
በመድኃኒትና የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ተገቢው ቁጥጥር መድረግ እንዳለበት እና ለዚህም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
 
በውይይቱ ከክረምቱ መውጣት ጋር ተያይዞ እየጨመረ ያለውን የወባ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top