ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ህብረት ሼህ መሐመድ አላሙዲንን ለኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥቷቸዋል።
ህብረቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ላለፉት 15 ቀናት ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ ቆይቷል።
በየሦስት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ በዘንድሮው ጉባኤው ላይ ከ3200 በላይ የምርምር ውጤቶች የቀረቡበት እና በአካል እና በበየነ መረብ የዓለም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
ህብረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት በሶስት አመት አንዴ ዕውቅና ይሰጣል፡፡
በዚህ መሰረት በዘንድሮው ጉባዔ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲን ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምረው ለኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ እድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ የክበር አባል እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲን በኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው ህብረቱ የክብር አበል እንዲሆኑ ዕውቅና የሰጣቸው፡፡
የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ የስልጠና እና ምርምር ማዕከል ሲቋቋም ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲን ከፍተኛውን አበርክቶ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ለህዋ ሳይንስ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ላባረከቱት አቶ ተፈራ ዋልዋ በአውሮፓውያኑ 2018 ቪዬና በተካሄደው ጉባኤ ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ህብረት እውቅና ሰጥቷቸዋል።
አለም አቀፉ አስተርኖሚካል ህብረት በአውሮፓውያኑ 1919 የተመሰረተ ሲሆን አለም አቀፍ ህዋ እና ጠፈር ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚወስን ከ85 አገራት በላይ እና ከ12 ሺህ በላይ ሳይንቲስቶችን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡