በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው የልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያየ

2 Hrs Ago 23
በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው የልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያየ

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተካተቱበት የልዑካን ቡድኑ ከዓለም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረገው በ2024 የባንኩ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ነው።

የልዑካን ቡድኑ በምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ እና በባንኩ ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አኪሂኮ ኒሺዮ ጋር ተወያይቷል። 

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የማክሮ-ኢኮኖሚ ተሃድሶ እንዲሁም፣ ቀጣይነት ያላቸው እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ እና በቀጣይ ትብብሮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ማዕከል ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያለበትን ደረጃ እና ከባንኩ በተገኘው ድጋፍ እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች በትክክል እየተተገበሩ መሆናቸውን በተመለከተ ለባንኩ ኃላፊዎች መረጃ ሰጥተዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቶቹ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መረጋጋት ለማምጣት በከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ደረጃ እየተወሰዱ ያሉትን የተሳኩ የፖሊሲ እርምጃዎችን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የዋጋ ንረትን ለማስተካከል እና በዘርፈ ብዙ ሴክተሮች ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረገችው ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።

የሥራ ኃላፊዎቹ ኢትዮጵያ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት እያደረገችው ያለውን ጥረት ለመደገፍ ባንኩ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top