ውጥረት በነገሰበት የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና እስራኤል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢራንን ጥቃት አላወገዙም በሚል ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አግዳለች።
የኢራን ጥቃት ከደረሰ በኋላ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቀጠናው ያለውን ግጭት መባባሱን ቢያወግዙም ኢራን ስለፈፀመችው ጥቃት ግን ምንም አለማለታቸው ተጠቅሷል።
ዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስተላልፈውት በነበረው መልእክት፤ በመከከለኛው ምስራቅ እየተስፋፋ ያለውን ግጭት አውግዘው፤ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በሰጡት መግለጫ፤ "ኢራን በእስራኤል ላይ ያደረሰችውን አሰቃቂ ጥቃት በማያሻማ መልኩ ማውገዝ የማይችል ማንኛውም ሰው የእስራኤልን ምድር መርገጥ አይገባውም" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን ወታደራዊ መሪ አባስ ኒሊፎሩሻን፤ የሀማስ መሪ እስማኤል ሃኒያህ እና በኢራን ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ እስራኤል በወሰደችው እርምጃ መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ ትላንት ምሽት የሚሳኤል ጥቃት ፈፅማለች፡፡
በእስራኤል ወታደራዊ ማእከላት ላይ ያነጣጠረው ጥቃቱ በመካከለኛው ምስራቅ በሁለቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በዓለም ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ እና ውጥረቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡
የኢራን መከላከያ ሀይል 110 የባላስቲክ ሚሳኤል፤ 30 የክሩዝ ሚሳኤል በእስራኤል ምድር ላይ ማስወንጨፉ የተገለፀ ሲሆን፤ የሚሳኤል ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ያደረሰው ጉዳት ስለመኖሩ ምንም የተገለፀ ነገር የለም፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ በፈፀመችው የአፀፋ ምላሽ 90 በመቶ ኢላማውን መምታቱን ብትገልፅም፤ እስራኤል ግን አብዛኛውን ጥቃት በአየር እንዲከሽፍ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡
እስራኤል በኢራን የተዋነጨፋበትን የሚሳኤል ጥቃቶች ዘመናዊ የአየር ላይ ጥቃትን መከላከል በሚችለው አይረን ዶም መከላከሏን ገልፃለች፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ ትላንት 180 ባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟልን ተከትሎ በርካታ የዓለም አቀፉ ማህበረሰረብ አካላት እና ሀገራት እርምጃውን በተመለከተ ድምፅ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፕዘሽኪን፤ የሀገራቸው ወታደራዊ እርምጃ እስራኤል በኢራን ላይ ለፈፀመቸው እርምጃ የመልስ ምት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታናሁ፤ ኢራን ትልቅ ስህተት ሰርታለች፤ የእጇን ታገኛለች በማለት ዝተዋል፡፡
የኢራን የሚሳኤል ጥቃት በቤተመንግንስታቸው ውስጥ በመቆጣጠሪያ ክፍል የተከታተሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ አሜሪካ ኤስራኤልን በሙሉ አቅሟ ትዳግፋለች ነው ያሉት፡፡
ሩሲያ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል በሰጠችው መግለጫ የኢራን-እስራኤል ግጭት የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር በመካከለኛው ምስራቅ የተከተለው ፖሊስ ውድቀትን የሳያል ብላለች፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ የምታስወነጭፈውን የሚሳኤል ጥቃታ ማቆሟን ብትገልፅም በቀጠናው ያለው ውጥረት ግን አሁን ቀጥሏል ሲሉ ቢቢሲ እና አልጃዚራ ዘግበዋል፡፡
በላሉ ኢታላ