የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በአፍሪካ ሕብረት ማለፍ ያለበትን ሂደት አልፎ ከዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት ገብቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት መግባት “የዓባይን ውኃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተደረገው ረጅም ጉዞ ፍጻሜ ነው” ብለዋል፡፡
የማዕቀፉ የልማት እና የትብብር በረከት
ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ ማግዊ ካውንቲ እና አጎራባቿ ኡጋንዳ በሚጋሩት ላምዎ በሚገኘው እና የናይል ገባር በሆነው ሊሙር ወንዝ ላይ ለመስኖ እና መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውሉ ሁለት ግድቦች ግንባታ ለመጀመር ማቀዳቸው ተገልጿል፡፡
የናይል ተፋሰስ ሀገራት ትብብር ኢኒሼቲቭ ህግ ለመሆን የሚበቃበትን ስምምነት በቅርቡ የፈረመችው የደቡብ ሱዳን ጥቅሙን ቀድማ ተረድታዋለች።
የደቡብ ሱዳን ውሃ ሚኒስትር የሆኑት ፓል ማይ ዴንግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረቡት ዕቅድ እንደገለጹት ሁለቱ ሀገራት በጋራ የሚገነቧቸው ግድቦች 98 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያወጣል።
"የሊሙር ባለብዙ ዓላማ ውሃ ሀብት ልማት ፕሮጀክት" በመባል የሚታወቀው ይህ ፕሮጀክት የመስኖ ልማት መርሐ ግብሮችን ለመደገፍ እና ለሰዎች እና ለእንስሳት የውሃ አቅርቦት የሚውል እንደሆነም ላይ ተጠቅሷል።
የሀገሪቱ የኢንፎርሜሽን ምክትል ሚኒስትር ማይጁ ኮሮክ በደቡብ ሱዳን የሚገነባው ግድብ 36 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያወጣ መገመቱን ጠቅሰዋል።
በናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሺቲቭ ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ በኡጋንዳ እና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገኘውና ግድቦቹ ይገነቡበታል የተባለው አካባቢ የአስዋ ተፋሰስ ባለፉት ዓመታት የግጭት፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ እና በርካታ ሰዎች የሚፈናቀሉበት አካባቢ እንደነበር የአይ ሬዲዮ ዘገባ ያመላክታል፡፡ ግድቦቹ አካባቢዎቹን በጋራ በማልማት የተጠቀሱትን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያው ቀውሶች ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ላይ ፕሮጀክቶቹን ለማካሄድ እንዲወስኑ ያደረጋቸው በቅርቡ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ ነው፡፡ ይህ የትብብር ማዕቀፉ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት አሸናፊ የሚያደርግ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ ማዕቀፉን በማጽደቅ ለተግባራዊነቱ የመሰረት የማዕዘን ድንጋዩን ያስቀመጠች የተፋሰሱ ሀገራት ባለውለታ ነች፡፡ የማዕቀፉን እንድምታ ቀጥለን እንመልከት፡፡
የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ አንድምታ
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ሁሉም አካላት በጋራ የሚጠቀሙበት የትብብር መድረክ እንዲኖር መንቀሳቀስ የጀመረችው በ1991 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ የተጀመረው የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ረቂቅን በማቅረብ ነው፡፡ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ የዓባይ (የናይል) ወንዝን የሚጋሩ ሀገራትን ያካተተ ቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፍ ነው። የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ ለኢትዮጵያ እና ወንዙን ሳይጠቀሙ ለረጅም ዘመናት ባይተዋር ሆነው ለኖሩት ሀገራት ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው የትብብር መድረክ ነው። ስምምነቱ ዘላቂ የውሃ አጠቃቀምን ለማስፈን በጋራ ለመስራት የሚያስችል እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየገነባቸው ያለችው ኢትዮጵያ በቀጣይ በወንዙ ላይ ለምትሠራቸው ፕሮጀክቶች በመተማመን እና ሌላውን በማይጎዳ መልኩ መሥራት ትፈልጋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ትብብርን የሚያስቀድመው ይህ ስምምነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለሚሄደው የኃይል ፍላጎቷ እና ለግብርና ልማት ዕቅዷ ወሳኝ የሆነ አግባብነት ያለው የውሃ መጠን ስለሚያስፈልጋት የዚህ ስምምነት መጽደቅ ይጠቅማታል።
ጊዜው ባለፈበት የቅኝ ግዛት ውሎች ላይ የተንጠለጠለችወ ግብፅ እና እሷን ተከትላ ወጥ አቋም መያዝ የተሳናት ሱዳን አሁን ወደ ስምምነቱ የሚመጡበት ጊዜ ነው፡፡ በ79ኛ የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ለግብፅ ክስ ምላሽ የሰጡት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ ጊዜው ግብፅ ሁሉን ተጠቃሚ ወደሚያደርግ መድረክ የምትመጣበት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት ለሀገራዊ ጥቅሟ ማእከል የሆነውን ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም በጋራ የመልማት ዓላማዋን የምታሳከበት ነው፡፡ በሌላ በኩል የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማክበር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መድረክም ነው፡፡ ይህ ትብብር ከውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን በመቀነስ መተማመን እና ትብብርን ይገነባል፡፡ እንዲሁም ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በወንዙ ላይ ሊሠሯቸው በሚያስቧቸው ፕሮጀክቶች ላይ የጋራ እና ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያደርግ ነው፡፡
የትብብር ማዕቀፉ ለተፋሰሱ ሀገራ ዘላቂ ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ወሳኝ የሆኑ የአየር ንብረት የመቋቋም እና የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶችን የሚደግፍ መሆኑንም ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በውሃ አቅርቦት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር በመሆን የውሃ አጠቃቀም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የውሃ አጠቃቀም ልማቶችን በማስተካከል ረገድ የትብብር እድልን ያሰፋላት። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዓባይ ወንዝ ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብፅ እና ሱዳን ቢያውቁበት ኖሮ የናይልን ውሃ ለመጠበቅ የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ይደግፉ ነበር ያሉት፡፡
ይህ ተሻጋሪ ትብብር ለድህነት ቅነሳ እና ለቀጣናዊ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የትብብር ማዕቀፉ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ተግዳሮቶችን በአንድነት በመፍታት የጋራ እድገትን እውን ለማድረግ ያላትን ፍላጎትም ማሳያ ነው።