የሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል፡፡
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ለ17ኛ ጊዜ በመላው ሀገሪቱ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦ በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበርም ምክር ቤቱ ጠቅሷል፡፡
ዕለቱ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢምባሲዎችና ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሥነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው፡፡
የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ ለብሔራዊ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ለሉዓላዊነትና ከፍታ እንዲሁም ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ እየተከበረ አስራ ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡