በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል አለው - ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ

18 Hrs Ago 192
በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል አለው - ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ

በአዋሽ ፈንታሌ እና ሳቡሬ ከተማ መካከል ላይ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል እንዳለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶክተር ኤሊያስ ሌዊ ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው የሀገራት ተሞክሮ እና ዘመኑ በደረሰበት የሳይንስ ደረጃ የመሬት መንቀጥቀጥ የት ይከሰታል እንጂ መቼ ይከሰታል የሚለውን እርግጠኛ ሆኖ መተንበይ እንደማይቻል ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ባለፈው ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ቀጥሎ ትናንት ምሽት 5፡11 ደቂቃ ላይ ዳግም ተከስቷል፡፡

የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲሆን አሁን ባለው መረጃ መሰረት በሬክተር ስኬል 4.8 አካባቢ እነደሆነም ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ለኢቢሲ ሳይበር አረጋግጠዋል።

በአካባቢው ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴው አሁንም እንዳልቆመ የገለፁት ዶ/ር ኤሊያስ፤ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም በመሬት ውስጥ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስካልቆመ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል እንዳለው ተናግረዋል።

በተለይም በአዋሽ ፈንታሌ እና ሳቡሬ ከተማ መካከል ላይ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ አሁንም መቀጠሉን ገልፀው፤ ይኸው የዓለት እንቅስቃሴ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ እየጨመረ የሚሄድበት እድል እንዳለም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው ተሞክሮ በ1983 ዓ.ም በዚሁ አዋሽ አካባቢ ከ 1 ወር በላይ የዘለቀ የመሬት መንቀጥቀጥ ተሰምቶ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ባለው የሳይንስ ደረጃና በበሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የት ይከሰታል እንጂ መቼ ይከሰታል የሚለውን መተንበይ እንደማይቻል ዶ/ር ኤሊያስ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ክስተት ጋር ተያይዞ እንደ ጃፓን ያሉ ሀገራት የመሬት መንቀጥቀጥ ከመከሰቱ 5 እና 10 ሰኮንድ በፊት የማስጠንቀቂያ መልእክት ማድረስ የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ይህ የመልእክት ማድረሺያ ስርዓት የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ የሚኖረው ሚና ያን ያህል የጎላ አለመሆኑንም ነው ዶ/ር ኤሊያስ የገለፁት፡፡    


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top