በኢትዮጵያ የጥጥ ልማትን ለማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚገባ ተጠየቀ

3 Hrs Ago 21
በኢትዮጵያ የጥጥ ልማትን ለማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚገባ ተጠየቀ
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣውን የጥጥ ልማት ለማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚገባ ተጠየቀ።
በአፋር ክልል በጥጥ ልማት የፋይናንስ አቅርቦት ላይ የተኮረ የውይይት መድረክ ከባለብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።
 
በጥጥ ልማት ዘርፍ የፍይናንስ አቅርቦት አለመሻሻል፣ከምርት አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የሰው ኃይል እጥረት፣ ከዘር አቅርቦት፣ ከገበያ አለማመቻቸት እንዲሁም ከተለያዩ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ባለሐብቶች ከዘርፉ እየወጡ እና ምርቱም እነቀነሰ መምጣቱን በክልሉ በዘርፉ በግል፣በድርጅት እና በማህበር እየሰሩ የሚገኙ ባለሐብቶች ገልጸዋል።
 
በውይይቱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ሌሎች የግል ባንኮች፤መንግስት አሁን ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሰጣቸው የግብርና እና ማዕድን ዘርፎች ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች እና ኢንቬስተሮች የብድር አማራጮችን በማቅረብ ሀገሪቷ በአፍሪካ ደረጃ ያቀደችውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመደገፍ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
 
በተጨማሪም ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ባንኮች የሚከተሉትን የብድር አመራጮች በማስፋት በተለይ በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ ባለሐብቶችን ለመደገፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
 
የኢትዮጵያ ጥጥ አልሚዎች እና መዳመጫዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ ኡዳ፤ከክልሉ አመራሮች ጋር በመነጋር ከመሬት፣ከሰው ኃይል እጥረትና ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ማህበሩ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
 
የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ኤይሻ ያሲን በበኩላቸው፤ ክልሉ በጥጥ ምርት የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በቅርቡ በተቋማት ላይ ለውጦች በማድረግ ኢንቬስተሮች አገልግሎት በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
 
በዘርፉ የሚታዩ የፋይናንስ፣የሰው ኃይል እና የዘር አቅርቦት ችግሮችን ለመፍተት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰሩ የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
 
በሁሴን መሐመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top