ፊፋ በኢትዮጵያ የወጣቶች ማዕከላት ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

3 Hrs Ago 24
ፊፋ በኢትዮጵያ የወጣቶች ማዕከላት ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ
በኢትዮጵያ የወጣቶች ስብዕና ማዕከላት በተሟላ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ እና የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።
 
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ስራ አስፈፃሚ አባል ኢሻ ጆሃንሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
ስፖርት በተለይም እግር ኳስ በአካል የዳበረ፣ጤናማ እና አምራች ዜጋ ለማፍራት ያለው ሚና ላይ በተለይ መክረዋል።
የአፍሪካ ሴቶች፣ሕፃናት እና ወጣቶችን ማብቃትና መደገፍ እንዲሁም ቀጣይ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።
 
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የወጣቶች ስብዕና ማዕከላት የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግ በዚህ ወቅት ጠይቀዋል።
 
የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ኢሻ ጆሃንሰን በበኩላቸው፥ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሰው፦ ለተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ አመስግነዋል።
 
ስፖርት የዜጎችን ትስስር ለማጠናከርና የማህበረሰብ ለውጥን ለማፋጠን ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
በስፖርቱ ዘርፍ እና በበጎ አድራጎት ስራ ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል።
 
ጆሃንሰን የቀድሞ የሴራሊዮን የእግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት፣ የፊፋ ምክር ቤት ብሎም የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፤ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሴት የእግር ኳስ ክለብ መስራችና ባለቤት እስከመሆን የደረሱ ናቸው።
 
የአፍሪካውያን ሴቶች ጤናን እየጎዱ ያሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭትን መከላከልና የጤና አገልግሎት ተደራሸነትን ማሳደግን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች አጋርነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ውይይት መደረጉ ተጠቁሟል።
 
በቀጣይ የባለብዙ ወገን ትብብርን በይበልጥ ማጠናከር እና ማሳደግ እንደሚገባ መገለጹን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
 
46ኛው የአፍሪካ እግር ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top