የኢኮኖሚ ማሻሻያው የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፍ እንዲል ማስቻሉ ተገለፀ

11 Hrs Ago 45
የኢኮኖሚ ማሻሻያው የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፍ እንዲል ማስቻሉ ተገለፀ

ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እየተገበረችው ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የኤክስፖርት ዘርፍ እንዲሻሻል፣ የአምራች ዘርፉ እንዲነቃቃ እና የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲያድግ ማስቻሉን የተለያዩ የባንክ አመራሮች ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የባንኩ የግል ሐዋላ በ62 በመቶ እንዲያድግ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

ይህም ትልቅ ለውጥ መሆኑን በማንሳት ልንደርስበት ካቀድነው ውጤት አንፃር ሲቃኝ ገና መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ማሻሻያው በጥቁር ገበያ እየታጣ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ወደ ባንኮች እንዲገባ አስችሏል ሲሉ የገለፁት የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ደረጄ ዘበነ ናቸው፡፡

አሁን ላይ በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መኖሩን የሚገልፁት አመራሮቹ ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ያለው የገዢዎች ፍላጎት መቀነሱን አመላክተዋል፡፡

በዚህም የውጭ ምንዛሬ ፈላጊዎች በባንኮች በኩል የሚፈልጉትን መጠን የውጭ ምንዛሪ በቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም ነው የገለፁት፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም ከባንኮች በተጨማሪ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ወደ ስራ እየገቡ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

በአፎምያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top