አፍሪካ በሳይበር ጥቃት ምክንያት ከዓመታዊ አጠቃላይ ምርቷ 10 በመቶ ልታጣ እንደምትችል ተገለፀ

17 Hrs Ago 55
አፍሪካ በሳይበር ጥቃት ምክንያት ከዓመታዊ አጠቃላይ ምርቷ 10 በመቶ ልታጣ እንደምትችል ተገለፀ

የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች  የሀገርንና የድርጅቶችን  ምስጥራዊ መረጃዎችን መውሰድ፣ አገልግሎትን ማስተጓጎል፣ የገንዘብ ስርቆት መፈፀም፤ በብሄራዊ ጥምቅ ላይ ጥቃት መፈፀም፣ የግለሰቦችንና የኩባንያዎችን ሀብት መዝረፍን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳቶችን እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡

በአፍሪካ በግልም ሆነ በመንስግታዊ ተቋማት እየጨመረ ያለው የሳይበር ጥቃት በተቋማት የስራ መስተጓጎል ከፍተኛ የገንዘብ ስርቆት፤ የምስጥራዊ መረጃዎች ስርቆትን ጨምሮ በርካታ ጉዳት ማድረሱን የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡

በአፍሪካ እየደረሱ ከሚገኙ የሳይበር ጥቃቶች መካከል ሀሰተኛ ኢሜልና ድረገፆችን ጨምሮ  ማህበራዊ የትስስር ዘዴዎችን በመጠቀም የድርጅቶችን መረጃና ገንዘብ ለመዝረፍ የሚፈፀመው ጥቃት ከፍተኛ መጠን እንዳለው ነው የተገለፀው፡፡

 

በአፍሪካ 90 በመቶ የሚሆኑት የንግድ ድርጅቶች የሳይበር ደህንነት መከላከል የሚያስችል ፕሮቶኮል የሌላቸው በመሆኑ ለጥቃት ታጋላጭ ናቸው ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ያላቸው ዝግጁነት አነስተኛ በመሆኑ ከዓመታዊ አጠቃላይ ምርት 10 በመቶ ሊያሳጣቸው እንደሚችልም ነው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው፡፡

ባለፉት 5 ወራት ብቻ በዓለም የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች ባለፉት 5 ዓመታት ከነበረው አንፃር በእጥፍ መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህን ጥቃት ለመከላከል በቂ የሳይበር ደህንነት መሰረተ ልማት አለመሟላት አንዱ ተግዳሮት መሆኑም ተነስቷል፡፡

በአህጉሪቱ አጠቃላይ የቢዝነስ ስራ ትልቅ ፈተና የሆነውን የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል  አህጉራዊ መፍትሄ መዘየድ አስፈለጊ መሆኑን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

በኢትዮያም በበዓላት ሰሞን ከፍተኛ ቅናሾችን የሚያቀርቡ የሚመስሉ የመስመር ላይ ገበያዎች፣ ከታመኑ ኩባንያዎች የሚመጡ የሚመስሉ የማስገር ኢ-ሜይሎች ወይም ጽሑፎች፣ እና ሀሰተኛ የሥራ/የውጪ ዕድሎች፤ የበዓል ጉዞ እና የመስመር ላይ (online) የአየር ትራንስፖርት ማጭበርበሮች በሳይበር ዘርፉ የሚደርሱ የጥቃት አይነቶች ናቸው፡፡

እንዲሁም ገንዘብ የሚሰርቁ ሀሰተኛ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ በሕዝብ ዋይ ፋይ (public Wi-Fi) በመጠቀም መጥለፍ አስጋሪ ማጭበርበሮች (phishing scams)፤ ኤቲኤም በሚጠቀሙበት ጊዜ የሚስጥር ቁጥርዎን መስረቅ ከተለያዩ የሳይበር ማጭበርበር መንገዶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሶፍትዌሮችን ወቅታዊ ማድረግ፤ ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፤ በሚታወቁ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ድረ-ገጾች ላይ ብቻ መገበያየት፤ አጠራጣሪ ነገሮችን በጥንቃቄ መመርመር አስፈላጊ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top