ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ባህሉን እና እምነቱን የሚገልጽበት የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ሐብት ነው

1 Day Ago 651
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ባህሉን እና እምነቱን የሚገልጽበት የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ሐብት ነው

የኦሮሞ ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ የገዳ ሥርዓት ያለው ሕዘብ ነው፡፡የገዳ ሥርዓት በውስጡ የአስተዳደር፣የእርቅ እና የምሥጋና ሥርዓቶችን የያዘ ነው፡፡

ሕዝቡ ከጥንት ጀምሮ አምላኩን ከሚያመሰግንባቸው እና ወግ እና ባህሉን ከሚያንጸባርቅባቸው በዩኔስኮ ከተመዘገበው የገዳ ሥርዓት መገለጫዎች አንዱ ኢሬቻ ነው፡፡

ትውፊቱን ጠብቆ የሚከበረው ኢሬቻ ታዲያ ከፍተኛ የቱሪዝም መስህብ ሊሆን የሚችል የሀገር ሐብት ነው፡፡

ይህም ኢሬቻን በምሥጋና ሥርዓትነቱም ሆነ በባህል ትሩፋትነቱ የህዝቡ አንድነት ማጠናከሪያ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ይህን ቱባ ባህል እንደ ትልቅ የሀገር ሐብት እንዲታይና ሀገር በቱሪዝሙ ከዚህ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ መሥራት ያስፈልጋል።

ኢሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት ተምሳሌትም ነው። ኢትዮጵያ በብዝሃ ማንነት፣ ባህልና  እሴቶች የደመቀች፣ በህብረ ብሔራዊነት የተጋመደች፣ወንድማማችነትን ከፍ አድርጋ ያፀናች ታላቅ ሀገር ናት።

ኢሬቻ ፍቅር፣ሰላም፣አንድነት፣ይቅር ባይነት ይበልጥ የሚፀኑበት ከኦሮሞ ቱባ ባህል የመነጨ ግዙፍ ክብረ በዓል ነው።

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ያሸጋገረውን አምላኩን የሚያመሰግንበትና መጪውን ዘመን የሰላምና የደስታ እንዲሆንለት የሚለምንበት በዓል ነው።

ኢሬቻ የአንድነት፣ የሰላም እና የወንድማማችነት ምልክት በመሆኑ ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው የሚያከብሩት፣ለሰላምና ወንድማማችነት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ የተነሳ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እየተሰራ ነው።

ኢሬቻ በየዓመቱ ሲከበር ብዙ ቱሪስቶች የሚመጡበት እና የሚታደሙበት እንዲሆን ማድረግም ይቻላል።

የኢሬቻ በዓል ከባህላዊ ትውፊቱ ባሻገር ለቱሪዝም ስህበት ከፍተኛ ሚና አለው የሀገራችንም ሆነ የመዲናችን አዲስ አበባ ገቢ ለማሳደግ አይነተኛ ድርሻ አለው፤ልንጠብቀው ይገባል።

በሌላ በኩል ሁሉም ማንነቱ፣ ሃይማኖቱ እና አመለካከቱ እንዲነካበት እንደማይፈልገው ሁሉ ኢሬቻንም እንደ ራሳችን መጠበቅ እና መንከባከብ እርስ በርሳችን ያለንን መተሳሰብ እና ወንድማማችነትን የሚገልጽ በጎ ተግባር ስለሆነ በዚህ ረገድ የማይታማው የኢትዮጵያ ሕዝብ የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ 

ኢሬቻን በተመለከተ የተዛቡ አመለካከቶች ይነገራሉ፤እነዚህ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመፍታት ሁሉም በሁሉም ቦታ ያለውን ባህል እና እምነት እንዲያከብር ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት ሕዝቡ ይህን ሥርዓት እንደ ሀገሩ ሐብት እንዲጠብቀው ማድረግ ያስፈልጋል።

ኢሬቻ ከማንኛውም ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ገለልተኛ የሆነ የህዝቡ ትውፊት መገለጫም ነው። ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሥርዓቱ አንዱ የኢትዮጵያ ጌጥ እንደሆነ አድርጎ መጠበቅ ያስፈልገዋል።

የገዳ ሥርዓት አንዱ መገለጫ የሆነው ኢሬቻ ከንጹህ ተፈጥሮ ጋር ተያይዞ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ሲሆን፣በመስከረም (ብራ) ክረምቱን አሳልፎ ለብርሃን ያበቃን ፈጣሪ የሚመሰገንበት፣በበልግ ደግሞ ፈጣሪ በጋውን አሳልፎ የበረከት ዝናብ እንዲያዘንብ የሚለመንበት ነው።

የ2017 የኢሬቻ በዓል ወንድማማችነታችንን እና አንድነታችንን ባከበረ፣ባህላዊ እሴቱን በጠበቀና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ አግባብ እንዲከበር ሁላችንም እንደወትሮው ሁሉ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣት ይገባናል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top