አባ መፍቀሬ ሰብዕ - ስማቸውን በተግባራቸው የለወጡት የሁሉ አባት

2 Hrs Ago 139
አባ መፍቀሬ ሰብዕ - ስማቸውን በተግባራቸው የለወጡት የሁሉ አባት

ከ73 ዓመታት በላይ ዛፎችን ሲተክሉ ኖረዋል። ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው ይባላል። "‘የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው’ ብለው ዛፍ ሲተክሉ እና ሲንከባከቡ ይኖራሉ" በማለት ነው ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሚገልጿቸው።

ተፈጥሮን አብዝተው በመንከባከብ፣ ችግኞችን በመትከል በርካታ ሰው ሰራሽ ደኖችን በመፍጠር  ይታወቃሉ የደሴው አባት አባ መፍቅሬ ሰብዕ።

 “መፍቅሬ ሰብዕ” ማለት ሰውን የሚወድድ በሰዎችም ዘንድ የሚወደድ ማለት ነው፡፡ አባ መፍቀሬ ሰብዕ የሚለው ስም የተሰጣቸው ከተግባራቸው ተነስቶ ነው፡፡ እሳቸው ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የሚወድዱ ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም ምክንያት ሁሉም ሰው ስለሚወዳቸው ስሙን ሕዝቡ አውጥቶላቸዋል፡፡ 

ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ አባ መፍቀሬ ሰብዕ በጻፉት ጽሁፍ፣ “ለእርሳቸው ዘርና ሃይማኖት ሰውን ለመርዳት መመዘኛዎች አይደሉም። ሰውነት ብቻ ይበቃቸዋል። ይህ ርዳታቸው ከመከራ ያወጣቸው፣ ከችግር የታደጋቸውና ሕይወታቸውን ያቀናላቸው ሰዎች ስለ እኒህ አባት ሲያወሩ ከማያቋርጥ ዕንባ ጋር ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ከንግግር ይልቅ እርሳቸውን እያሰቡ ዝም ብለው በማልቀስ ይገልጧቸዋል። መቼም ለአንዳንዱ አብዝቶ አይደል የሚሰጠው። እርሳቸው የአካባቢ ጥበቃ አርበኛም ናቸው" ብለዋል።

ሙዓዘ ጥበባት ስአባ መፍቅሬ ሰብዕ የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ ሲገልጹ በአድናቆት ነው፡፡ በእርጅና ዕድሜያቸው እንኳን መቆፈሪያ እና መኮትኮቻ፣ አካፋና ባሬላ ይዘው በደሴ ተራሮች ላይ ዛፍ ሲተክሉ እንደሚውሉ ነው የሚገልጹት፡፡ 

በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ያላቸው ንቁ ተሳትፎ በድፍን የደሴ ከተማ ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ አድርጓቸዋል፡፡ የታመመ መጠየቅ፣ የሞተን መቅበር፣ ሀዘን መድረስ፣ በደስታ ጊዜ መገኘት፣ በበዓላት “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህዝባዊ በዓላት ላይ በማስተባበር እና በማስተማር የሚያደርጓቸው ተሳትፎዎችም መቼም ከሕዝቡ ልብ እንዳይጠፉ አድርጓቸዋል።

ውልደታቸው ሰሜን ሸዋ ልዩ ስሙ ተጉለት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሲሆን፣ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ ደሴ ከተማ ኖረዋል፡፡ ደሴን ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ በተግባራቸው በፍቅር የገዙት አባ፣ “የደሴ ከተማ ህዝብ ከህዝበ ክርስቲያኑ ባልተናነሰ ሙስሊሙ ማኅበረሰብም ለኔ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ይገልጽልኛል፤ ያገኙኝ ሁሉ 'አላህ ረዥም እድሜ ያኑርህ' እያሉ ይመርቁኛል” በማለት የደሴ ሕዝብ ለሳቸው ስላለው ፍቅር ተናግረዋል።

የደሴ ሕዝብም ይህንኑ ነው የሚመሰክረው፡፡ አባ መፍቅሬ ሰብ ሰውን በሃይማኖቱ እና በማንነቱ ሳይመዝኑ በደስታውም ይሁን በሀዘኑ ጊዜ ፈጥነው ከጎኑ በመገኘት 'አይዞህ' የሚሉ አባት እንደሆኑ የደሴ ነዋሪዎች ይናገራሉ። በሃይማኖቶች እና በአማኙ መካከልም መተባበር እና መከባበር እንዲኖር የሠሩት ሥራ በሁሉም ልብ እንዲታተሙ አድርጓቸዋል።

ከዕድሜያቸው ከ70 ዓመታት በላይ ከሃይማኖት ትምህርት ጎን ለጎን ዛፍ በመትከል እና ተፈጥሮን በመንከባከብ አሳልፈዋል። ዛፎች መትከል የጀመሩት በቤተ ክርስቲያን ጊቢ ውስጥ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያታቸውን ሲገለጹ ሰዎች ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ ማረፊያ እንዲያገኙ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን በጎ ተግባራቸውን ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውጭም አስፋፍተው መላውን ደሴን አረንጓዴ ለማድረግ ተግተዋል፡፡

ከዛፎች ጋር ያላቸው ቁርኝት የጀመረው ጎንደር ውስጥ አገልግሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ ደን ያለአግባብ ሲጨፈጨፍ ባዩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከ1943 ዓ.ም ጀምሮ "ደን መጠበቅ አለበት" በሚል ሀሳብ ዛፎችን መትከልና መንከባከብ ጀመሩ።

ለምን ዛፍ መትከል ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ሲናገሩ፣ “የደን መጨፍጨፍ ለተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች ይዳርጋል። ዝናብ ይጠፋል፣ ድርቅ ይከሰታል፣ ሙቀት ይጨምራል። በመሆኑም ያለአግባብ ዛፍ የሚቆርጡትንና ደን የሚጨፈጭፉትን ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ በተለያየ ጊዜ ትምህርት እሰጣለሁ። ከዚህ አልፈው በእኩይ ተግባራቸው የሚቀጥሉትንም የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ እገዝታቸዋለሁ” ብለዋል።

በደሴ ከተማ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አብዛኛዎቹን አስተባብረው ካሰሯቸው አባቶች መካከል አባ መፍቀሬ ሰብ ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡ አባ አብያተ ክርስቲያናትን መገንባት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ማናቸውም የልማት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡መልካም ተግባሮቻቸውን በተለይም ዛፍ መትከልን ለብዙ ደቀ መዛሙርቶቻቸው አውርሰዋል፡፡

አባ መፍቅሬ ሰብዕ ከተከሏቸው ደኖች መካከል በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ቅጥር ግቢ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። የገዳሙን ቅጥር ግቢን የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል አካባቢውን ባለበሱት ግርማ ሞገስ፣ በጣም ማራኪ፣ የዓይን ማረፊያ እና የመንፈስ ምግብ ብሎም የቱሪስት መስህብ መሆኑ ለታላቅ ተግባራቸው ቋሚ ምስክር ሆኖ ይኖራል።

ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የሚሄዱ ምዕመናንን ስቃይ የተረዱት አባ መፍቀሬ ሰብዕ የአካባቢውን ባለሥልጣናት በማነሳሳት እና ሕዝቡን በማስተባበር በ1973 ዓ.ም 17 ኪሎ ሜትር የተራራ መንገድ እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ ይህ ተግባራቸውም ብዙ ምዕመናንን ከነፍሳቸው ምኞት ጋር አገናኝቷል፡፡

አባ ስለ ዛፎች ሲናገሩ፣ “ዛፎቼ እንደሰው የማወራቸው ልጆቼም ጭምር ናቸው። ከእነርሱ ጋር በምሆን ሰዓት ሳልበላ ሁሉ እጠግባለሁ” ይላሉ። 

የደሴ ከተማ ማኅበረሰብም እሳቸው ያለውን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ ገንዘብ አዋጥቶ ወጪያቸውን ችሎ ሃይማኖታዊ ጸሎት እንዲያደርሱና ጉብኝት እንዲያደርጉ ወደ ኢየሩሳሌም እና ግብፅ ደርሰው እንዲመጡ አድርጓቸዋል።

መጠሪያ ስማቸውን በተግባራቸው የቀየሩት አባ መፍቀሬ ሰብዕ ከሰው ሁሉ እና ከተፈጥሮ ጋር በፍቅር ኖረው፣ ፈጣሪያቸውን በተግባር አገልግለው በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

በለሚ ታደሰ

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top