ኢትዮጵያ የካፍ ጠቅላላ ጉባኤን ማዘጋጀቷ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንድታገኝ እንደሚያስችላት ተገለፀ

8 Hrs Ago 33
ኢትዮጵያ የካፍ ጠቅላላ ጉባኤን ማዘጋጀቷ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንድታገኝ እንደሚያስችላት ተገለፀ

ኢትዮጵያ 46ኛውን የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ማዘጋጀቷ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንድታገኝ ያስችላታል ሲሉ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ዶ/ር ወንድወሰን ተፈራ ተናገሩ።

ስፖርት በተለይም እግር ኳስ ትልቅ የስበት ማእከል ነው ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን፤ በጉባኤው የሀገራችንን አቅም ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ረቂቅ ቀርቦ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህም የሚዘጋጀው ሰነድ የካፍ ደረጃን መሰረት ያደረገ እና በጉባኤው ላይ ቀርቦ አባል ሀገራቱን በማሳመን የአዘጋጅነት ውሳኔ እንዲያገኝ የሚመለከታቸው አካላት መስራት አለባቸው ብለዋል።

የካፍ አባል ሀገራትን ለማግባባት የጉብኝትና ሌሎች ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው ያሉን የስፖርት መሰረተ ልማቶች መታየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በቀሪው 5 አመታትም ሁሉም የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንደሚጠናቀቁ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ በቂ መንገድና ትራንስፖርት እንዳለን ማሳየት ይገባል ብለዋል።

ዶ/ር ወንድወሰን ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በጉባኤው በሚቀርቡ ሰነዶችና ተያያዥ ስራዎች በካፍ አባል ሀገራት ላይ የራስን ተጽዕኖ አሳድሮ የ2029 አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት እድሉን ለመውሰድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ይደረጋል።

በሁሴን ግዛው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top