"ኢትዮጵያ ብዙ ሆና አንድ፣ አንድ ሆና ደግሞ ብዙ ነች፤ የዚህ መገለጫው ደግሞ ሰንደቅ ዓላማችን ነው" - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

1 Day Ago 145
"ኢትዮጵያ ብዙ ሆና አንድ፣ አንድ ሆና ደግሞ ብዙ ነች፤ የዚህ መገለጫው ደግሞ ሰንደቅ ዓላማችን ነው" - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከበረው 17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ እንዳሉት ሰንደቅ ዓለማ የብሔራዊ አንድነታችን እና ሕብረታችን ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅር እና ብሔራዊ ስሜት መገለጫ፣ ታሪካዊ ማኅበራዊ ትስስራችን እና የሥነ-ልቦናዊ አንድነታችን የሚንፀባረቅበት ምልክት ነው፡፡

ሰንቅ ዓለማ የመስዋዕትነት፣ የነጻነት፣ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ዓርማ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የአንድነታችን፣ የሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን መገለጫ ታላቅ ሀገራዊ እሴት፣ የአብሮነታችን፣ ዓርማ ምልክትም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንታቸውን አፍስሰው፣ ውድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው፣ በክብር አስጠብቀው፣ በክብር ያስረከቡን በልባችን ታትሞ የቆየ የአሸናፊነትና የነጻነት ዓርማችን ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ታፍራ እና ተከብራ የቆየች ታላቅ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗንም አውስተዋል፡፡

በመንግሥታዊ አስተዳደር ሥርዓትም ቢሆን በጣም ረጅም ዓመታት ካስቆጠሩት ቀዳሚ ሀገራት ተርታ የምትጠቀስ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ የሰንደቅ ዓላማ ታሪኳም ከሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ጋር በእጅጉ የተቆራኘና የተሳሰረ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ሀገራዊ ነጻነታችንና ሉዓላዊነታችንን ለመንጠቅ በየዘመናቱ በተደጋጋሚ የመጡ የውጭ ወራሪ ኃይሎችን እናት አባቶቻችን በተባበረ ክንድ በአንድነት ቆመው መክተውና አሳፍረው የመለሱት ለሀገራቸው እና መለያቸው ለሆነው ሰንደቅ ዓላማ ከሚሰጡት ክብር እንደሆነ አስታውሰው፣ ይህም ከፍቅር እና ብሔራዊ ስሜት በመነሳት እንደሆነ ሁላችንም ከቀደምት ታሪካችን የምንረዳው ነው ብለዋል፡፡

ስለዚህም የሀገራችን ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማችን እስከ ዛሬም ጸንቶ የቆየው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በከፈሉት መስዋዕትነት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኛ በኢትዮጵያውያን ብቻ ታትሞ የቆየ ብሔራዊ መለያችን ብቻም ሳይሆን በአፍሪካውያን እና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የነጻነትና የእኩልነት ንቅናቄ ዓርማ ምልክት ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም በርካታ አፍሪካውያን ሀገራት፣ አንዳንድ የካሪቢያን ሀገራት እና ንቅናቄዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላመ ቀለማት ለሰንደቅ ዓላማቸው ሊጠቀሙበት ችለዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ማንኛም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር ሊሰጥና እንደ ብሔራዊ በዓል ሊያከብረው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ቀን ትርጉም ባለው መልኩ ማክበር ለብሐሔራዊ መግባባት፣ ለአብሮነታችን፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት መጽናት እጅግ አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም፣ "ኢትዮጵያ ብዙ ሆና አንድ፣ እንድ ሆና ደግሞ ብዙ ነች፤ የዚህ መገለጫ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማችን ነው፤ እንደ ሀገር ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እንዲሁም የኢትዮጵያን ከፍታ አስተማማኝ መሰረት ላይ ለማኖር የምንችለው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ በማድረግ በተሰማራንበት ሥራ ሁሉ ጠንክረን በመሥራት ነው" ብለዋል፡፡

ከትላንት እስከ ዛሬ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በደማቸው ሉዓላዊነቷንና ነጻነቷን አስጠብቀው ያኖሯትን ሀገር እኛ ዛሬ በዕውታችን፣ በጉልበታችን እና በላባችን በማልማት ያሉብንን የዘመናት እዳዎች ወደ ሀብት በመቀየር በታላቅ ተስፋና ነገን በማለም በአብሮነት ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ ከፍታ ከመቼውም በበለጠ ለመሥራት መነሳት እንደሚኖርብንም ተናግረዋል፡፡

ሉዓላዊነታችን የተሟላ የሚሆነው ሀገራችንን ከልመና ነጻ ማውጣት ስንችል ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ ይህ ትውልድ ያለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ተገንዝቦ በየተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ በዕውቀቱና በላቡ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ መረባረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የዛሬው ትውልድ የራሱ የጋራ አሻራ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በአንድ ልብ፣ በአንድ ሀሳብ፣ በራሱ ዕውቀት፣ ጥረትና ላብ ገንብቶ በማጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንደተወጣ ሁሉ በቀጣይነትም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ከፍተኛ ኃላፊነቱ ነውም ብለዋል፡፡

በዚህች በዛሬዋ ዕለት የሀገራችንን ህልውና ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን የመከላከያ፣ የፀጥታ እና ሌሎች ሠራተኞችን በማክበር በአንጻሩ ደግሞ ሀገራችንን ለማዳከም የሚሠሩና በከንቱ ምኞቶቻቸው ሀገራችንን የሚያውኩትን ኋላ ቀር ምኞቶቻቸውን በማምከን ለሰንደቅ ዓላማችን ክብር በመቆም ታሪካዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top