ኢትዮጵያ የጀመረችው የቁም እንስሳትን በባቡር ወደ ውጭ የመላክ ስራ ከውጭ ሀገራት ከፍተኛ ፍላጎት እየታየበት መሆኑን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ፡፡
ኢንጂነር ታከለ ኡማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ከአዳማ ወደ ጂቡቲ የቁም እንስሳት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ ጋር ተያይዞ ለወደፊት ብዙ የቁም እንስሳትን ለማስተናገድ እየተሰራ ያለውን የማስፋፊያ ስራ መጎብኘታቸውን ገልፀዋል።
ከመጀመሪያው የቁም እንስሳትን በባቡር የመላክ ስራ በኋላ ከውጭ ሀገራት ከፍተኛ ፍላጎት መምጣቱን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህንን እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት የአቅም ማስፋፊያ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ የማስፋፊያ ስራ ላይ በበዓላት ቀን ጨምሮ እየሰሩ ለሚገኙ ሰራተኞች ኢንጂነር ታከለ ኡማ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዳማ ወደ ጂቡቲ የቁም እንስሳት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡