ዓለም ብዙ ባያወራለትም ቀደምት ስልጣኔዎች የነበሩባት በተፈጥሮ ሀብቶች የበለፀገች ዛሬ ዓለም ደረስኩበት ከሚለው ስልጣኔ ባልተናነሰ የአክሱምን ስልጣኔ የመሰሉ ስልጡን የነበሩ ህዝቦችና መንግስታት የነበሩባት አፍሪካ ተጠቃሽ ነች።
የአፍሪካን ጥንታዊነትና ቀደምት ስልጣኔ የሚያመላክቱት እና ለዚህ ትውልድ ከሚያወሱት መካከል ደግሞ ከሺህ ዓመታት በፊት የነበሩ ከተሞቿ ተጠቃሽ ናቸው። እስቲ በእድሜያቸው መርጠን ጥቂቶቹን መለስ ብለን ለመመልከት እንሞክር።
- ሉክሶር (ቴብስ) ግብፅ
በአፍሪካ ውስጥ በጣም ዝነኛ ከሆኑት ጥንታዊ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ የግብፅ ከተማ የሆነችው ሉክሶር (ቴብስ) አንዷ ነች። ይህቺ ከተማ የ5200 ዘመን እድሜ እንዳላት ይገመታል።
የቴብስ ከተማ ላይ ተመርኩዘው የተፃፉ የታሪክ መዛግብት እንደሚያመላክቱት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3 ሺህ እስከ 2 ሺህ ባለው ጊዜ ውስጥ ከተማዋ በጣም ፈጣን እድገት ያስመዘገበች ከተማ ስለነበረች የግብፅ ግዛት ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች።
ከተማዋ በመቄዶንያውያን፣ በኋላም በሮማውያን፣ በአረቦች እና በኦቶማኖች እጅ ወድቃም ነበረ። ከዓመታት በኋላ የአሙን-ራ አምላክ መናገሻ ከተማ በመሆን የግብፅ የሃይማኖት ቀጠና ሆና ቆይታለች።
ዛሬ ላይ ሉክሶር (ቴብስ) የ1.3 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ስትሆን በግብፅ ካሉ ከተሞች አምስተኛዋ ትልቅ ከተማ እና በርካታ አስደናቂ ታሪካዊ ስፍራዎች መገኛ ነች።
- ካርቴጅ (ቱኒዚያዋ)
የ2 ሺህ 9 መቶ ዓመታት ዕድሜ ባለቤት የሆነችው ከተማ ካርቴጅ ቱኒስ በአፍሪካ ውስጥ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ነች። ከተማዋ በሰሜን አፍሪካ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኝ እና ማዕከላዊ ቦታ ላይ በመሆኗ በፍጥነት ወደ ክልላዊ የንግድ ማዕከልና ከዚያም የመንግሥት መቀመጫ ሆናለች።
የፑኒክ ጦርነት ከተካሄደባት በኋላ ካርቴጅ በሮም ተያዘች። ከመካከለኛው ዘመን በኋላ ካርቴጅ የኦቶማን ግዛት አካል በመሆን በ19 ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በፈረንሳይ ሞግዚትነት መተዳደር ጀመረች።
ዛሬ ላይ የካርቴጅ ከተማ ቅሪት በቱኒዝያ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሰፈር ብቻ ሆኗል። ነገር ግን አካባቢው አስደናቂ የአርኪኦሎጂ ቦታዎች ስላሉት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ አድርጓታል።
- ታንጊር (ቲንጊ) ሞሮኮ
አትላንቲክ ውቅያኖስ ከሜዲትራኒያን ባህር ጋር በሚገናኝበት ከጅብራልታር ባሕር በስተምዕራብ በማግሬብ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ታንጊር ከተማ በአፍሪካ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ናት።
ታንጊር ከተማ የጀመረችው በ10ኛው ክፍለ ዘመን ነበር። ጥሩ የመልክዓምድራዊ አቀማመጧ በሰሜን አፍሪካ ውስጥ በብዛት ከሚዘወተሩ የንግድ ማዕከሎች አንዷ ሆና እንድታገለግል አድርጓታል።
ከተማዋ በመጨረሻ በሮማውያን ቁጥጥር ስር ዋለች። ነገር ግን በሰዓቱ ልዩ የማዘጋጃ ቤት መብቶችንም አግኝታ ነበር። ከሮም ውድቀት በኋላ ታንጊር የባይዛንታይን ግዛት አካል ሆኖ እስከ አረቦች ወረራ ድረስ ቆይታለች። በኋላም ለስፔን ወረራዎች የሎጂስቲክስ መሰረት ሆና አገልግላለች።
ከመካከለኛው ዘመን በኋላ በታንጊር አካባቢያዊ አቀማመጥ ምክንያት የአውሮፓ ኃያላን ለእሷ መፎካከርን ቀጠሉ እና ከተማዋ በፖርቱጋል፣ ብሪታንያ እና ስፔን እጅ ብዙ ጊዜ ቆይታለች።
ታንጊር በ 1956 ሞሮኮን በመቀላቀል ዛሬ ከሀገሪቱ ዋና ዋና የቱሪስት ማዕከሎች እና በጣም አስፈላጊ ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች።
- ትሪፖሊ (ኦያት) ሊቢያ
ከሊቢያ ሰሜናዊ ምዕራብ በሜዲትራኒያን ባህር በረሃው ዳርቻ ላይ የምትገኘው ትሪፖሊ የ2 ሺህ 7 መቶ ዓመት ባለጸጋ ስትሆን የሊቢያ ዋና ከተማ ነች።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ7ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በፊንቄ ቅኝ ግዛት ስር ኦያት በሚል ስም የተመሰረተችው ይህች ከተማ ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ ከተማይቱ በግሪኮች የቂሬናይካ ገዥዎች እጅ ገባች። በ 1ኛው ክፍለ ዘመን የዓክልበና የሮማ ግዛት አካል ነበረች።
ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ከተማዋ በስፔን እና በኦቶማን ኢምፓየር እንዲሁም በጣሊያን ቁጥጥር ስር ወድቃ ነበር።
በሰሜን አፍሪካ ከሚገኙ ግዛቶች መካከል የባርበሪ ግዛቶች አካል የሆነችው ትሪፖሊ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከ1969 ጀምሮ የሊቢያ ዋና ከተማ ሆና እያገለገለች ትገኛለች።
- ኢፌ ናይጄሪያ
በአፍሪካ ውስጥ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ስትሆን ከተመሰረተች 2 ሺህ 5 መቶ ዓመታትን አስቆጥራለች።በአህጉሪቱ ውስጥ ደግሞ በሸክላ ሴራሚክስ፣ በመዳብ-ቅይጥ እና በነሐስ ጌጣጌጦች ስራ የምትታወቅ ከተማ ነች ኢፌ።
በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ኦሱን ግዛት ውስጥ የምትገኝ ጥንታዊቷ ኤፌ የተመሰረተችው በዮሩባ በ500 ዓመት አካባቢ ሲሆን ለዓመታት የግዛቱ ቅድስተ ቅዱሳን ከተማም ትባልም ነበረ። በዮሩባ ሃይማኖት መሰረትም የሰው ልጆች መገኛ እንደሆነች የሚታመንባት ቦታ ነበረች።
ከተማዋ ያደገችው በ2ኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን በ16ተኛው ክፍለ ዘመን የወደቀውና ታላቅ የነበረው የኢፌ ኢምፓየር ዋና ከተማ በመሆንም አገልግላለች። ስሟንም ከዚሁ ኢምፓየር ነው የወሰደችው።
ዛሬ ኢፌ ከተማ ወደ 5 መቶ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ ናት ይህም በናይጄሪያ 16ኛዋ ትልቅ ከተማ አድርጓታል።
- መንደፈራ ኤርትራ
መንደፈራ በአፍሪካ ከሚገኙት ጥንታዊ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ከተማዋ የተመሰረተችው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው እና በ4ኛው ክፍለ ዘመን መካከል በዲምት መንግስት ሲሆን ለአክሱማዊ ስልጣኔ በጣም አስፈላጊ ከነበሩት ከተሞች አንዷ በመሆንም አገልግላለች።
ባለፉት አመታት መንደፈራ በኦቶማን ኢምፓየር፣ በአውሳ ሱልጣኔት በኋላም በጣሊያን እና በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወድቃ ተዳድራለች።
ዛሬ መንደፈራ ከአፍሪካ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ብትሆንም እንደ ቀድሞው ትልቅ ቦታ የላትም። 2 ሺህ 5 መቶ ዓመታትን ያስቆጠረችው ከተማዋ የንግድ ማዕከል እና የ63 ሺህ ሰዎች መኖሪያ በመሆን በኤርትራ አራተኛዋ ትልቅ ከተማ ያደርጋታል።
- በርበራ ሶማሊላንድ
በርበራ በራስ ገዝ በሆነችው ሶማሌላንድ የሳሂል ክልል ዋና ከተማ እና በህንድ ውቅያኖስ ውስጥ ካሉ የባህር ወደቦች አንዷ ናት።
ከተማዋ ከጥንት ጀምሮ የነበረች ሲሆን ለሶማሌ ጎሳዎች ከመጀመሪያዎቹ የከተማ-ግዛቶቻቸው አንዷ ነች።
የዛሬ 2 ሺህ 4 መቶ ዓመታት የተመሰረተችው በርበራ ባላት አቀማመጥ ምክንያት የምንጊዜም የሶማሊያ በጣም አስፈላጊ የንግድ ማዕከልም ናት ትባላለች።
ከጥንት ጀምሮ ከተማዋ ከፊንቄ፣ ከጥንቷ ግሪክ፣ ከቶሌሚክ ግብፅ፣ ከፓርቲያን ፋርስ እና ከሮማ ኢምፓየር ጋር የንግድ ግንኙነት ነበራት።
ከአረቦች ወረራ በኋላ ከተማይቱ ሙሉ በሙሉ የአረቦች ሆና ነበር በዛም የተነሳ መልኳ በጣም ተለወጠ። በመካከለኛው ዘመን ከተማዋ በአብዛኛው በተለያዩ የሙስሊም መንግስታት ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ድረስ በብሪታንያ እጅ ስር ቆይታለች።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በበርበራ ከተማ የሚካሄደው የንግድ ልውውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀንስም ከተማዋ አሁንም ካሉት አስፈላጊ ወደቦች አንዷ እና የሶማሊያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ነች።
- አክሱም ኢትዮጵያ
የዛሬ 2 ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያ የስልጣኔ መሰረት ብሎም ከዓለም ትልልቅ ስልጣኔዎች አንዱ የሆነው የአክሱም ስልጣኔ ግንባር ቀደም ነው።
አክሱም በአፍሪካ ካሉት ጥንታዊ ከተሞች አንዷም ነች። ከተማዋ ከጥንት ክርስትና በፊት ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ዋና የባህር ኃይል እና የንግድ ማዕከል ነበረች።
በ354 ዓ.ም ክርስትናን እንደ ሀይማኖት ከተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ የአክሱም መንግስት አንዱ ሲሆን የሙስሊም መንግስታት የሰሜን አፍሪካን ድል እስካደረጉበት ጊዜ ድረስ ግዛቱ በአካባቢው የበላይ ሃያል ነበረ።
ከ7ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የቀይ ባህርን የንግድ መስመሮች አረቦች እና ፋርስ ከወሰዱት በኋላ ግዛቱ ቀስ በቀስ ማሽቆልቆል ጀመረ።
ከ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ከተማው ገናናነቷን ብታጣም ጥንታዊው ስልጣኔ ያረፈባቸው ሀውልቶቿ እና ዛሬም ድረስ የሚጠኑት የአርኪኦሎጂ ቦታዎቿ የጥንት ውበቷን ይዘው ለምስክርነት ቆመዋል።
የአክሱም ሀውልት በዩኔስኮ በአለም ቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል።
- ሞምባሳ ኬንያ
በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ የምትገኘው ሞምባሳ በታሪክ ውስጥ ከዋና ዋና የአፍሪካ የክልል የንግድ ማዕከላት አንዷ ስትሆን 1 ሺህ 2 መቶ ዓመታት ያስቆጠረች ነች።
በይፋ ከተማዋ ከ900 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ የምዋና መኪሲ (ስዋሂሊ) ሥርወ መንግሥት ከተማዋን እንደመሰረታት ይነገራል።
ባለፉት ዓመታት ሞምባሳ ህንድን፣ ፋርስን እና የአረብ ባሕረ ሰላጤን ከስዋሂሊ ሕዝብ ጋር ከሚያገናኙት በጣም አስፈላጊ የንግድ ማዕከሎች አንዷ ሆኖ ኖራለች።
- ላሊበላ ኢትዮጵያ
ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩ ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገለጫዎቿ የሆኑት ላሊበላ ከተማ የተመሰረተው በ12ኛው እና በ13ኛው ክፍለ ዘመን መካከል የዛሬ 800 ዓመት መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሲሆን ላሊበላ የአፍሪካ እየሩሳሌም እየተባለ እንዲጠራ አስችሎታል።
ጥንታዊ ሆነው ታሪክና ባህል በጋራ ይዘው የቆዩ አሁንም ድረስ ያሉ እንዳሉ ሁሉ ታሪካቸውን ለፃሀፊያን ትተው የጠፉ አፍሪካዊ ከተሞችም አሉ። እኛም አሁን ድረስ ለዓይን በሚታይ መልኩ ስልጣኔያቸው አብረዋቸው ያሉ 10 ከተሞችን ነው ያስቃኘናችሁ።
በናርዶስ አዳነ