የፖሊዮ ሕመም

3 Days Ago 157
የፖሊዮ ሕመም

የፖሊዮ በሽታ ምንነትን በሚመለከተ እንዲያስረዱን የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ሚኪያስ አላዩ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

እንደ እርሳቸው ገለጻ፥ የፖሊዮ ሕመም በፖሊዮ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት የእግር፣ የእጅ እንዲሁም የውጭ ክፍልን የሚያልፈሰፍስ በሽታ ነው። በሽታው የነርቭ ሴሎችን በመጉዳት ሌሎች አካሎች እንዳይታዘዙ እንደሚያደርግም ሐኪሙ ይናገራሉ። 

የፖሊዮ በሽታ በዋናነት ህጻናትን የሚያጠቃ ሲሆን፤ በብዛት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ እና በዋናነት ደግሞ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ያጠቃል ብለዋል። ይሁን እንጂ አዋቂዎች ላይም ሊከሰት እንደሚችል ሐኪሙ ይናራሉ። 

ፖሊዮ ሲይዝ በፍጥነት የእግር ወይም የእጅ መልፈስፈስ እንደሚያጋጥም አንስተዋል። በተፈጥሮ የሚከሰት የፖሊዮ በሽታ እና ያልተከተቡ ልጆችን የሚይዝ የፖሊዮ በሽታ መኖሩን ጠቅሰው፤ የተፈጥሮ የፖሊዮ በሽታ ህጻናት በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ የሚከሰት እንደሆነ ገልፀዋል። 

ፖሊዮ ከመከሰቱ በፊት በጣም ጥቂት ምልክቶችን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ ከምልክቶቹም፡-

  • ኃይለኛ ትኩሳት እንዲሁም
  • የእጅ እና የእግር መልፈስፈስ ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል። 

ለዚህ ሕመም የሚሰጠው መከላከያ በዘመቻ መልክ የሚሰጠው ክትባት እንደሆነ አውስተው፣ በሽታው ከያዘ በኋላ ሳይዛመት በፊዚዮቴራፒ እንደሚታከምም አንስተዋል። ነገር ግን በሽታው አንዴ ከያዘ ሙሉ በሙሉ እንደማይድንም ዶክተር ሚኪያስ አላዩ አክለው ገልፀዋል። 

ፖሊዮ የሚተላለፈው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ባለ ንክኪ፣ በተበከለ ምግብ እና በተበከለ ውሃ ስለመሆኑ ያብራሩት ሐኪሙ፤ ንጽህናን መጠበቅ በሽታውን ለመከላከል አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ ከክትባት በዘለለ አመርቂ የመከላከያ መንገድ አለመኖሩን ይናገራሉ።

በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ በማስከተብ የፖሊዮን በሽታ እንዲከላከሉ እንደሚችሉ ዶክተር ሚኪያስ ይመክራሉ። 

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top