ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና ለ3ኛ ጊዜ ተመርጣለች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት አንደኛ ፀሐፊ (ከፍተኛ ዲፕሎማት) ኩራባቸው ትርፌሳ ዛሬ በኒውዮርክ በተካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ከሚያስፈልጋት 97 ድምጽ 171 ድምጽ ማግኘቷን ገልጸዋል።
በምርጫው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይ የተመድ 193 አባል አገራት መሳተፋቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከጥር 1/2025 አንስቶ እስከ 2027 ለሶስት ዓመት የምክር ቤት አባል ሆና እንደምታገለግል ጠቁመዋል።
ቤኒን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ እና ኬንያ ከአፍሪካ የምክር ቤቱ አባል ሆነው መመረጣቸውን ነው ፀሐፊው የገለጹት።
ቦሊቪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ አይስላንድ፣ ሜክሲኮ፣ ኳታር፣ ሰሜን ሜቄዶኒያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ታይላንድ፣ ስፔን፣ ኮሎምቢያ፣ ቆጵሮስ እና ማርሻል አይላንድስ ሌሎች የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡ አገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከእ.አ.አ 2013 እስከ 2015 እንዲሁም ከእ.አ.አ 2016 እስከ 2018 የምክር ቤቱ አባል ሆና ማገልገሏን አስታውሰዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ለጣሉባት እምነት እና ለሰጧት ድጋፍ ኢትዮጵያ ምስጋናዋን ማቅረቧንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ አባልነቷ የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መብቶች በዓለም ላይ እንዲከበሩ አበክራ እንደምትሰራም ነው ያመለከቱት።
በተጨማሪም ለታዳጊ አገራት የሚሰጡ የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፎችን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራም ተናግረዋል።