ባለፉት 6 ዓመታት 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም መልማቱ ተገለፀ

6 Days Ago 156
ባለፉት 6 ዓመታት 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም መልማቱ ተገለፀ

ባለፉት 6 ዓመታት 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም መልማቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዝላታን ሚሊሲክ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ለዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ የግብርና ስራን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና የኢትዮጵያን አንድ ሶስተኛ አጠቃላይ እድገት፣ ሁለት ሶስተኛውን ኤክስፖርት እንዲሁም 65 በመቶ የገቢ ምንጭ እንደሚሸፍን አመልክተዋል።

25 በመቶ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሜካናይዜሽን እየተጠቀሙ እንደሚገኝ እና ባለፉት 6 ዓመታት 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም መልማቱን ተናግረዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከሰብዓዊ እርዳታ ባሻገር ዘላቂነት መፍትሔ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ 95 ከመቶ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ድርጅቱ የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር እየተከናወነ ባለው ስራ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዝላታን ሚሊሲክ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ በምግብ ዋስትና በኩል ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህንኑ እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በመስኖ ልማትና በሌሎች ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በእህል ጎተራ ስራ፣ በእሴት መጨመር፣ በድህረ ምርት አያያዝ፣ በግብርና ኢንሹራንስ እና በቴክኖሎጂ ድጋፍ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top