እንኳን ሰው ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ያሆዴ”

2 Hrs Ago 13
እንኳን ሰው ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ያሆዴ”

በሀዲያ ብሔር ተወላጆች ዘንድ ያለምንም ልዩነት በአንድነት የሚከበረው “ያሆዴ” የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ እና በልዩ ድምቀት ከሚከበሩ ቱባ በዓላት አንዱና ቀዳሚው ነው።

የሀዲያ ህዝብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለው ሲሆን "ያሆዴ" በዓል ደግሞ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት የሚቀበልበት ነው።

ያሆዴ ከአዲስ ተስፋ፣ ከልምላሜ፣ ለሀገር ሰላም ፀሎት ከማድረግ፣ ከብርሃን ጋር የሚገናኝ ተደርጎም ይወሰዳል። በዓሉም የክረምቱ ጭጋግ፣ ወንዝ መሙላት አልፎ በመጸው መባቻ የሚከበር እንደመሆኑ መጠን ብሩህ ተስፋ የሰነቀ፣ የብርሃን ጮራ ያዘለ የመልካም ምኞት ማሳያ በዓል መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ታዲያ እንዲህ ያለውን በዓል ለማድረስ ሁሉም የየራሱንዝግጅት ያደርጋል። ከዛም በጋራ ሆኖ በደስታ በዓሉን ያከብራል ፈጣሪውንም ያመሰግናል።

የ”ያሆዴ” በዓል ሲነሳ ሁሌም አብሮ የሚነሳው ያ ሆዴ ጭፈራ (ጨዋታ) ነው። ጭፈራውን ወጣት ወንዶች በአካባቢያቸው ተሰብስበው በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምሽቱን ሙሉ የሚጨፍሩት ነው።

በዚህ ዕለት ማታ ፉኒታ ( ሆያ ሆዬ) የሚጨፈርበትና ጨፋሪዎች ደግሞ "ከዚህ ቤት ችጋር ይውጣ፣ በሽታ ይውጣ!" ብለው ችቦ እያቀጣጠሉ ሁነቱን የሚያደምቁበት ነው። በዚህ መንገድ መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባወራና እማወራ ደግሞ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁና ይሸኟቸዋል።

በየገቡበት ቤት ሁሉ አተካና እና ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግቦችን እየበሉ የቤቱን አባወራንና እማወራ ይመርቃሉ። ለዚህ በዓል ሴቶችም ከአለባበስ እስከ ፀጉር አሰራር ድረስ በጥንቃቄ ተውበው የብሔሩን ቱባ ባሕል ጠብቀው ይዘጋጃሉ።

የሀገር ሽማግሌዎች ተሰልፈው ስርዓቱን ያስጀምራሉ፣ ይከታተላሉ፣ ይመርቃሉ። የሀዲያ ብሔር እሴት የሆነው ያሆዴ ከነሀሴ ወር ጀምሮ በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነው። በዚህ በዓል ሴቶች ቀደም ብለው ስራቸውን ይጀምራሉ። ቤታቸውን ያዘጋጃሉ። በህብረት ስራ ይሰራሉ።

ወንዶች ደግሞ እንጨት ያዘጋጃሉ፣ ሰንጋ ይገዛሉ፣ ህፃናት ጦምቦራ (ችቦ) ቀድመው ይሰራሉ። በያሆዴ ሰው ብቻ ሳይሆን ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት በመሆኑ ከአምስት ወር ጀምሮ ጥብቅ ወይም ክልክል ሳር ይፈቀድላቸዋል።

በዓሉ ከመከበሩ በፊት ከሚከናወኑ ዋና ዋና ክንውኖች ጥቂቶቹን እንመልከት፦

#የእርቅ_ሥነ_ሥርዓት

ያሆዴ የተጣላ ታርቆ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ በመተሳሰብ እና በፍቅር መጪውን አዲስ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት በመሆኑ፣ አስታራቂዎችም ቂም ይዞ አዲስ ዓመትን መቀበል አይቻልም በማለት የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቃሉ።

በሀዲያ አዲስ ዓመትን ያሆዴን ለመቀበል በቅድሚያ አንድ ሰው ከተጣላው ጋር እርቀ ሰላም ማውረድ አለበት። ቂም ይዞ አዲሱን ዓመት መቀበልም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ዝግጅት ማድረግ አይችልም።

ለዚህም ሲባል የብሔሩ የሀገር ሽማግሌዎች በየአካባቢው እየዞሩ የተጣላን ያስታርቃሉ። የተጣሉ ሕፃናትም ቢሆኑ ተፈላልገው በሚታረቁበት በዚህ ወቅት በማህበረሰቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲኖር ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።

ከዚህ በዓል ማግስት ጀምሮ የሀዲያ ህዝብ የመረዳዳት ባህሉን በስፋት የሚያንፀባርቅበት፣ በአዲስ መንፈስ በማህበረሰቡ መካከል ግንኙነትን በማጠናከር እንደ ቤተሰብና እንደ አካባቢው እቅዶች ተለይተው የሚታረቁበት፣ እንደ ማህበረሰብ እንዴት መለወጥ እንዳለባቸው የሚመካከሩበትና አቅጣጫ የሚይዙበት በመሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ ጥቅሙ የጎላ ነው።

በልማት፣ በግብርና፣ በንግድና በሌሎች ስራዎች ላይ የሚመክሩበት በዓል ነው። ለስራው ባለው ትጋት እንደምሳሌነት የሚጠቀሰው የሀዲያ ህዝብ ለስራ ከተሰማራባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከሀገር ውጭም ሳይቀር ያሆዴ በዓልን ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከአብሮ አደግና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለማክበር ወደ ሀዲያ ይተማል።

በአሉን ለማክበር በወርሀ መስከረም መግቢያ ላይ ወደ ሀዲያ ምድር የሚተመው አውቶቡስ፣ ሚኒባስ የግል መኪና ቁጥር በቀላሉ ሊጠቀስ የማይችል ነው። ይህ እውነታም በሙዚቃና በሥነ ቃል ጎልቶ ይታያል።

ያሆዴ ያ ሆዴ ያሆዴ…… ያሆዴ ሆ ያሆ

ዱቢንሴ ኢንጃ ጉሎ………ዴ ሆ ያሆ

ባሪንሴ ዋሳ ጉሎ………..ያሆዴ ሆ ያሆ በማለት ያዜማሉ። ትርጓሜውም ከጓሮ ቅመም ጨራሽ ከጉድጓድ ቆጮ ጨራሽ እንደማለት ነው።

#መቻዕል_ሜራ (የእብድ ገበያ)

የእብድ ገበያ አንዱና ዋነኛው የ ያሆዴ በዓል ከሚከበርበት ዕለት ከአስራ አምስት ቀናት አስቀድሞ የሚጀመረው “የመቻዕል ሜራ”  የበዓል ዝግጅት የሚደረግበት ገበያ ነው።

መቻዕል ሜራ የሚለውን ቃል ሀሳቡ የእብድ ገበያ እንደማለት ነው። በያሆዴ የእብድ ገበያ አንዱ አካል ነው።

ይህ ስርአት በብሔሩ ባህላዊ አንድምታ ያለውና የገበያ ተጓዦች ስርአት ሲሆን፤ ከትውልድ ቀያቸው እርቀው የሚኖሩትን የማህበረሰብ አካላት ሳይቀር የሚያገናኝ የበዓል ገበያ ነው። በዚህ ገበያ ፈጣሪ ይመሰገናል።

ሁሉም ሰው ገበያውን ይጎበኛል። ታዲያ በዚህ የዕብድ ገበያ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም። ገበያ ገብቶ የለም የሚባል ቃል አይሰማም። ስያሜውም የእብድ ገበያ እንደመሆኑ ከሌሎች የገበያ ቀናት የሚለየው የራሱ የሆኑ በርካታ መገለጫዎችና ክንዋኔዎች አሉት።

የእብድ ገበያም የሚል ስያሜ ያሰጠው ገበያው የሚደራበት ሰዓት ከወትሮው የተለየ በመሆኑ ነው። በዚህ ወቅት ጊዜ ውድ በመሆኑ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገበያው በመድራቱ ነው። በዚህ ሰዓትም መገበያየት ይጀመራል።

ሌላው ደግሞ እንደመደበኛ እስከ ማታ አለመቆየቱ ነው። ከቀኑ በስድስትና በሰባት ሰዓት ሰው ተገበያይቶ ገበያው ይበተናል።

ይህም ገበያ የሀዲያ አባቶች "ጊዜውን እንዴት እንጠቀም" በሚል በባህላዊ ጥበብ የተቀነባበረ የጊዜ አጠቃቀምን የሚያሳይ ነው። በዚህ ገበያ አባወራ በእብድ ገበያ ከቀረቡ ሰንጋዎች መካከል መርጦ ቀልቡ ያረፈበትን ሙሉ ብር እንኳን ባይኖረው ገዝቶ የሚወስድበት የግብይት ሥርዓት ነው።

ምንም ብር ከሌለው ደግሞ ከመጣበት አካባቢ የአንዱን ታዋቂ ሰው ስም በመጥራት ቀልቡ ያረፈበትን ሰንጋ ያለ ምንም ተያዥ ይዞ ይሄዳል። ቀሪውን ብር ደግሞ በአዝመራ ወቅት ይከፍላል።

በዚህም መሰረት ለያሆዴ የወሰዱትን ሰንጋ ከህዳር እስከ ጥር ባለው ወራት ውስጥ በታማኝነት ተከፍሎ ያልቃል። በዕብድ ገበያ እናቶች ለያሆዴ በዓል አተካና ለማዘጋጀት የሚጠቅሙ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን የእንሰት ተዋፅኦ ያዘጋጀሉ።

#አተካና

በዓሉን አስመልክቶ የሚኖረው ቅድመ ዝግጅት ለያሆዴ ክብረ በዓል አንዱ የሆነው የአተካና ወይም የአተካኒሞ ምሽት ነው። ያሆዴ አንድ ተብሎ መከበር የሚጀምረው አተካኒሞ ከበዓሉ አንድ ቀን በፊት አዛውንቶች ችቦ በማቃጠልና አተካናን በመቅመስ ነው።

አተካና የሀዲያ ባህላዊ ምግብ ነው። በብዛት የሚዘጋጀው ለያሆዴ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ለእንግዳ የሚቀርብ ነው። አሰራሩም በጥንቃቄና በስርአት ሲሆን ከተሰራ በኋላ ከአንድ ወር በላይ መቆየት ይችላል። በያሆዴ አተካናን አለማዘጋጀት አይቻልም።

የሚሰራው ከቆጮ፣ ቡላ፣ ቅቤ፣ አይብ፣ ወተትና ከተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ነው። ስራውም አድካሚና ጥራትን ስለሚፈልግ ቀደም ብሎና በሕብረት መሰራት ይጀምራል።

በዚህ ሥራ ላይ እንሰት ፍቆ ቡላ ከማዘጋጀት አንፃር በተለየ ሁኔታ ልጃገረዶች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። አተካና የዘመን መለወጫ ቀንን አመላካች ነው። በበዓሉ እለት ለሚመጣ እንግዳና ማታ ለጭፈራ ለሚመጡ ህፃናት አተካና የግድ ይሰጣል።

በአቅም ምክንያት አተካናን እንኳን ማዘጋጀት የማትችል ሴት ካለች የአካባቢው ነዋሪዎች ለአተካና መስሪያ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማጠራቀም ይሰጣሉ። በአሉም የሁሉም ሰው ደስታ ሆኖ እንደሚያልፍ ከሀዲያ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top