የሃማስና የእስራኤል ጦርነት ከ11 ወራት በፊት ከጀመረ ወዲህ በእስራኤል ውስጥ ከታዩት ትልቁ የተባለለት ተቃውሞ ትላንት እሁድ ምሽት ተጀምሯል።
በጋዛ ስድስት እስራኤላውያን ምርኮኞች በሀማስ መገደላቸውን ተከትሎ የእስራኤል የሰራተኞች ህብረት የስራ ማቆም አድማ ጠርቶ ነው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጎዳና በመውጣት ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩት።
ወደ አደባባይ የወጡት እስራኤላውያን በመጨረሻም “ጦርነት በቃን የተኩስ አቁም ስምምነትን ይደረግ” የሚል ጥያቄንም አንስተዋል።
በዚህ ተቃውሞ ላይ የተሳተፉ ዜጎች በምዕራብ እየሩሳሌም በሚገኘው የኔታኒያሁ ቢሮ አጠገብ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚገኙ ምርኮኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ አሁኑኑ ከፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በታቃውሞው ላይ በጋዛ የታሰሩትን ቤተሰቦች የሚወክለው የታጋቾች እና የጠፉ ቤተሰቦች ፎረም የስድስቱ ታጋቾች ሞት የተከሰተው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኒታኒያሁ ጦርነቱን ለማስቆም ታጋቾችን ለማስፈታት ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው የመጣ ነው በማለት ኮንነውታል።
ለ11 ወራት በሀማስ ተይዘው የነበሩና አሁን ሕይወታቸው ማለፉ የተሰማው ስድስት ምርኮኞች ሲሆኑ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው በፍልስጤም ግዛት ውስጥ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 101 መሆኑንና 35 ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።
በስራኤል እና ሃማስ መካከል ያለው ጦርነት በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ቀን ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል የጦርነት ይብቃ ጥያቄዎች እንዲህ በሰፊው ሲሰማ የመጀመሪያው ሆኗል።
ሆስፒታሎች ፣ የጤና አጠባበቅ ማእከሎች፣ ድንገተኛ አደጋ ሰጪ ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች ሲቀሩ ሌሎች ሰራተኞች የተሳተፉበት የተባለው ሀገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ በመንግስት ላይ ጫና ማድረግ ካልቻልን ሌሎች ታጋቾችንም በህይወት አናገኛቸውም በሚል እየተካሄደ ነው ተብሏል።
ይሁን እንጂ የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ማቆም አድማውን የተቀላቀሉ ሰራተኞች በአሰሪዎች በኩል ደሞዝ እንዳይከፈላቸው አስታውቋል።
እስራኤል ከሃማስ ጋር ወደ ሰላም እንዳይመጡ ዋና ምክንያት ነው የተባለው የፊላዴልፊ ኮሪደር ሲሆን 14 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው አካባቢ ጋዛን ከግብፅ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ የሚገኝ እና አሁኑ የእስራኤል ጦር የሚቆጣጠረው ነው።
በመጀመሪያው የስምምነት ምዕራፍ እስራኤል የድንበር ዞኑን ለመቆጣጠር የጠየቀች ሲሆን ሃማስ ግን የእስራኤል ወታደሮች መውጣት አለባቸው ብሏል።
ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሃማስ ከሥሩ ባሉ ዋሻዎች የሚያደርገውን የጦር መሳሪያ ዝውውር እንደገና እንዳይጀምር ኮሪደሩን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ነው የሚያምኑት ተብሏል።
በዚህ አለመግባባት ውስጥ ታዲያ ታጋቾችን ለመልቀቅ የነበረው ተስፋ እየጨለም ነው የሚሉ ቤተሰቦች እና አሁን ላይ ደግሞ ብዙዎች የተቀላቀሉት የህዝብ ጥያቄ የሆነው።
አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ ስምምነቱን ለመፍጠርና ለማደራደር ወራትን ያሳለፉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኔታንያሁ በፊላዴልፊ ኮሪደር ላይ የበለጠ ተለዋዋጭ እንዲሆኑ ግፊት ማድረጋቸውም ተሰምቷል።
ዛሬ ላይ ሰላም ይውረድ ብለው በቴልአቪቭ ጎዳናዎች የወጡት እስራኤላውያን በጥቅምት 7 ታግተው ለሞቱት ዜጎች ሃማስን ተጠያቂ ቢያደርጉም፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለችግሩ አለመፈታት ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።
ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ በተቀሰቀሰው ጦርነት በትንሹ 40 ሺህ 738 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 94 ሺህ 154 ቆስለዋል ነው የተባለው።
በእስራኤል በበኩል ደግሞ 1 ሺህ 139 ሰዎች ሲገደሉ 250 ሰዎች በሃማስ መታገታቸውን ቢቢሲና ሲኤንኤን ዘግበዋል።
በናርዶስ አዳነ