ጳጉሜን የሀገራችን ልዩ ወር ናት፤ 13ኛ ወር። ከተለመደው የምዕራባውያኑ የአንድ ዓመት የ12 ወራት ዑደት የኛዋ ጳጉሜን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት አምስት ቀናት፣ በየአራት ዓመቱ ደግሞ ስድስት ቀን ሆና ትከሰትና ወደ አዲሱ ዓመት ታሻግረናለች። በሕግም ሆነ በውል የሚፈጠሩ መብትና ግዴታዎች ብዙውን ጊዜ ከጊዜ ገደብ ጋር የተያያዙ ናቸው። በወር አቆጣጠር የተቀመጡ የውል የጊዜ ገደቦችን በተመለከተ ከጳጉሜን አንፃር ሕጋችን ምን እንደሚል እናያለን።
የጳጉሜን ትርጓሜ
በደስታ ተክለ ወልድ የተጻፈው እና በ1962 ዓ.ም የታተመው ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ጳጉሜን "የወር ስም፥ 13ኛ ወር፥ ተረፈ ዓመት፥ በነሐሴ መጨረሻ በሦስት ዓመት አምስት ቀናት፥ በአራተኛው ዓመት ስድስት ቀን የሚሆን ትርጓሜውም ጭማሪ ማለት ነው" ሲል ይተረጉመዋል።
የጳጉሜን ወር በውል ውስጥ
የሕግ ወይም የውል ግዴታዎችን ለመወጣት ወይም መብትን ለመጠቀም የጊዜ አቆጣጠር በቀናት፣ በወራት ወይም በዓመታት ሊቀመጡ ይችላሉ።
ውሎችን በተመለከተ ከተደረጉበት ቀን ጀምሮ ወይም በውሉ ላይ ተዋዋዮች ካስቀመጡት ቀን ጀምሮ ተዋዋዮች እስከ ቆረጡት ቀን ግዴታቸውን መወጣት ወይም መብታቸውን መጠቀም የሚችሉበትን ጊዜ መወሰን ይችላሉ። ይህ የተወሰነ ጊዜ እንዴት ይቆጠራል? የሚለው ውሉ ላይ በግልፅ ካልተቀመጠ አለመግባባትን ሊያስነሳ ይችላል።
ውሎችን በተመለከተ ውሉ ከተደረገበት ወይም በውሉ ላይ ከተቀመጠው ቀን አንስቶ የሚቀመጠው ጊዜ እንዴት መቆጠር እንዳለበት በፍትሐ ብሔር ሕጋችን ከቁ.1857 -1868 ድረስ ያሉት አንቀፆች ይደነግጋሉ።
የቀናት አቆጣጠር
በቀናት ተገድቦ የተቀመጠ ጊዜ በውል ውስጥ ካለ ዕዳው ወይም የሚፈፀመው ግዴታ ውሉ የተደረገበትን ቀን ሳያካትት ወይም ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ በመቁጠር የመጨረሻው ቀን ላይ ግዴታው የበሰለበት ወይም ያ ቀን ካለፈ ውል እንደማፍረስ ሚቆጠርበት ቀን ይሆናል።
የሳምንት አቆጣጠር
የውሉ ጊዜ የተጠቀሰው የጊዜ አቆጣጠር በሳምንት ከሆነ ደግሞ ውሉ ላይ በስም ከተጠቀሰው ቀን ጋር ተመሳሳይ ቀን ላይ በሚውለው የመጨረሻ ሳምንት ላይ ግዴታው በስሏል ማለት ነው። ለምሳሌ ሰኞ ዕለት ውሉ ተደርጎ ግዴታው ከአራት ሳምንት በኋላ እንዲፈፀም ከተስማሙ የውሉ መፈፀሚያ የመጨረሻው ቀን አራተኛው ሳምንት ላይ ሰኞ ዕለት ይሆናል ማለት ነው።
የወራት አቆጣጠር
ጊዜው የተገለፀው በብዙ ወራት ከሆነ ደግሞ ግዴታው የሚበስለው የመጨረሻው ወር ላይ ከሚውለው እና ውሉ ከተደረገበት ቀን ጋር ተመሳሳይ በሆነው ቀን ላይ ነው። ለምሳሌ በወሩ 10ኛ ቀን ላይ የተደረገ የስድስት ወር ውል የሚበስለው በስድስተኛው ወር በ10ኛው ቀን ላይ ነው።
የአውሮፓውያን ቀን አቆጣጠር
ጊዜው የተቀመጠው እንደ አውሮፓውያኑ ቀን አቆጣጠር ከሆነ እና በመጨረሻው ወር ውስጥ ያሉት ቀናት መጨረሻ ላይ ውሉ ከተደረገበት ቀን ጋር ተመሳሳይ ቀን ከሌለ በመጨረሻው ወር የመጨረሻው ቀን ላይ ውሉ እንደበሰለ ይቆጠራል። ይህም የሆነው በአውሮፓውያኑ ቀን አቆጣጠር ውስጥ 12ቱ ወራት እኩል ቀናት ስለሌላቸው ነው።
ጳጉሜን በውል ውስጥ
የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1860(3) ጳጉሜን በስሟም ባይሆን በወር ተራ ቁጥሯ ጠቅሶ በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር 13ኛዋ ወር በወራት በተቀመጠ የውል ጊዜ አቆጣጠር ውስጥ እንደ ወር ተቆጥራ ከግምት እንደማትገባ ይደነግጋል።
ይህም ጳጉሜያችን በእኛ ቀን አቆጣጠር መሰረት በወራት የጊዜ ስሌት ለተቀመጠ ውል እንደወር አትቆጠርም ማለት ነው። ይህ ድንጋጌ ከውል የሚመነጩ መብት እና ግዴታዎቻችን ላይ ያስከተለውን ውጤት ለማሳያነት እንጠቅሳለን። ለምሳሌ የሥራ ውላችን በኛ ቀን አቆጣጠር የተደረገ የወር ደሞዝተኛ ከሆንን ለጳጉሜን ወር የወር ደምወዝ አይከፈለንም። የቤት ኪራይም በኛ አቆጣር በየወሩ ለመክፈል ተስማምተን ብንከራይም ለጳጉሜን የቤት ኪራይ አንከፍልም። ጳጉሜን ከውል ጋር በተያያዘ እንዲህ ናት።
ለማንኛውም መልካም አዲስ ዓመት!!
ኪዳኔ መካሻ ለኢቢሲ ሳይበር እንደጻፈው