በስልጤ ዞን ከ6ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ነዋሪዎች ጠየቁ

4 Mons Ago 1222
በስልጤ ዞን ከ6ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ነዋሪዎች ጠየቁ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ስልጢ እና ምስራቅ ስልጢ ወረዳዎች በሚገኙ ከፍተኛ ስፍራዎች ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የሚፈጠረው ጎርፍ ማረቆ ወረዳን አቋርጦ በኦሮሚያ ክልል በመቂ አልፎ ወደ ዝዋይ ሀይቅ ይቀላቀል ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ለመስኖ በሚል በማረቆ ወረዳ ከዓመታት በፊት የተሰራው የመስኖ ግድብ  በከፍተኛ ደለል በመሞላቱ ምክንያት ውሃው መውራጃ ሲያጣ በአካበቢው እየተፈጠረው ያለው የጎርፍ አደጋ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡

ሰሞኑን ስልጤ ዞን ስልጢ እና ምስራቅ ስልጢ ወረዳዎች ከ6 ቀበሌዎቸ በላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ እስከሁን ከ9 መቶ በላይ ቤቶች በጎርፍ ሲዋጡ፤ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡

የስልጤ ዞን ኮሚኒኬሽ ሃላፊ አቶ ሳሊ ሃሰን በተለይም ለኢቢሲ ሳይበር አንዳሉት በአደጋው ምክንያት ከ1200 ሄክታር በላይ የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና ምርት ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡

የጉዳቱ ሰላባ ከሆኑት መካከል አንዱ ኡመር ስርሞሎ ለኢቲቪ እንደተናገሩት ውሃው በየቀኑ እየጨመረ ነው፤ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በውሃ ተውጠዋል፤ የአከባቢው ነዋሪዎች ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ በአከባቢው የነበሩ ከ6ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅዋል ብለዋል፡፡

የተከሰተው ከባድ ጎርፍ ነው፤ እስከሁን በእድሜያችን አይተነው አናውቅም፤ የተፈናቀለው ማህበረሰብ ውሃ ባልደረሰበት በአከባቢው በሚገኝ ት/ቤቶች፤ ኤፍቲሲ እና ግማሹ ዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልሏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የአደጋው ሰለባ አቶ መሀመድ አማን በበኩላቸው፤ ጎርፉ ከቤታችን ከንብረታችን አፈናቅሎናል፤ ቋሚና ጊዜያዊ ሰብሎችም ተብላሽተዋል፤ የቤት አንስሳት መኖ፣ እህል፣ የበቆሎ ማሳ እንዲሁም ከቋሚ ሰብሎች ፓፓያ፣ ቡና፣ ማንጎ፣ ሙዝ ሁሉም ደርቋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የጎርፍ አደጋው ድንገት የተከሰት በመሆኑ የአከባቢው ነዋሪ ህይወቱን ከማትረፍ ውጭ ምንም ዓይነት ንብረት ማዳን አለመቻሉን የገለፁት ነዋሪዎች፤ በአደጋው ጉዳት የደረሰበት ነዋሪ አሁን ላይ የሚበላውና የሚጠጣው ስለሌለው ለረሃብ እየተጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአከባቢው በበጎ ፍቃድ የተሰማሩ ወጣቶች፤ ወረዳው ዞኑ ድጋፍ እየደረገ ቢሆንም የተጎጂ ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ መላው ኢትዮጵውያን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የስልጤ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሳሊ ሃሰን የጎርፍ አደጋው ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ምን እየተሰራ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የጎርፍ ውሃ መውረጃው ላይ የተፈጠረውን ደለል ለማስተካከል የክልልና የፌደራል መንግስት በጋራ ከ5 ዓመታት በፊት 63 ሚሊዮን ብር መድቦ ደለሉን የማውጣት ስራ የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን አለላቀም ብለዋል፡፡

በተሰራው ደለል የማውጣት ስራ ባለፉት 2 ዓመታት አርሶ አደሮቹ እፎይታ አግኝተው እንደነበረም አውስተዋል፡፡

በአደጋው ሙሉ በሙሉ ንብረታቸው ያጡ የአከባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋው ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top