ግላዊ የአደገኛነት መጠን እና የትምህርት ደረጃ በወንጀል ቅጣት ላይ

19 Hrs Ago 197
ግላዊ የአደገኛነት መጠን እና የትምህርት ደረጃ በወንጀል ቅጣት ላይ

የወንጀል ፈፃሚው ግላዊ የአደገኝነት መጠን እና የትምህርት ደረጃው በወንጀል ቅጣት መጠን ላይ የሚኖረውን ውጤት እና የወንጀል ሪከርድ አለመኖር በከባድ ወንጀል ጥፋተኝነት ላይ ቅጣት ማቅለያ ሊሆን አለመቻሉን በተመለከተ ፌደራል ሰበር ድረስ ደርሶ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ የተሰጠበትን አሳዛኝ የወንጀል ድርጊት እናያለን።

መምህሩ በመምህሩ ላይ

ቢንያም ማሞ(ዶ/ር) እና አቶ አበባየሁ ዮሴፍ የአንድ ዩንቨርስቲ የመምህራን ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት ትምህርት የሚሰለጥኑ ተማሪዎችን ያስትምሩ ነበር። ቢንያም ማሞ(ዶ/ር) አንድ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ሊያሳትም መሆኑን አቶ አበባየሁ ሳሙኤል ያውቃል። አቶ አበባየሁ ግን መንፈሳዊ ቅናት አድሮበት እሱም በሙያው ወይም በሌላ መስክ እንደ ዶክተር ቢንያም ዕውቀቱን በመጠቀም ፅፎ ለህትመት ለማብቃት ከመትጋት ይልቅ የዶክተር ቢንያምን ዕውቀት ዘርፎ የራሱ አስመስሎ ለማቅረብ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ተመካከረ።

2ኛ ተከሳሹም ገንዘብ ከተከፈለው መጽሐፉን በእጁ እንደሚያስገባለት አረጋገጠለት። 1ኛ ተከሳሽ አበባየሁም የተጠየቀውን ክፍያ ለመክፈል ተስማማ።2 ኛ ተከሳሽም ሌሎች አራት ተከሳሾችን ለታቀደው የወንጀል ተግባር መለመለ።

አጥማጇ ሜሮን

ከነዚህ ተመልማዮች አንዷ ሜሮን የምትባል ስትሆን የሷ ሚና ዶ/ር ቢንያምን ቀርባ በማግባባት ሌሎች የአበባየሁ ግብረበሮች ወደ ሚፈልጉት ቦታ ማምጣት ነበር።

ሜሮን በተሰጣት የአጥማጅነት ሚና መሰረት ዶክተር ቢንያምን ቀርባ ተግባባችው። አጥምዳውም የታቀደለት ግፍ ለሚፈፀምበት ቀን አዘጋጅታው የአበባየሁ እና የግብረ አበሮቹን ትዕዛዝ ትጠብቅ ጀመር። የምትጠብቀው ትዕዛዝም "በዚህ ቀን እዚህ ቦታ አምጪው እስከዚህ ሰዓትም እንዲቆይ አድርጊው" የሚል ነበር።

የመጀመሪያው ዕለት

የሚጠበቀው ዕለት ደረሰ። ይህ ዕለትም ነሐሴ 20 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር። ሜሮን ለዶክተር ቢንያም ደወለች። አግባብታውም የመጀመሪያው ወንጀል ሊፈፀም ወደታቀደበት ቦታ አብረው ሄዱ። እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓትም አብረው ቆዩ። ይሄን የሜሮንን ግዳያቸውን አጥምዶ የማመቻቸት ተግባር በንቃት ሲከታተሉ የነበሩት አበባየሁ እና ግብረ አበሮቹም የሜሮን እገዛ ከእንግዲህ አያስፈልጋቸውምና ሜሮን ጉዳዩን የማታውቅ አስመስለው ያቀዱትን ሊፈፅሙ ተንቀሳቀሱ።

የአበባየሁ እና አራት ግብረ አበሮች ዶክተር ቢንያምን አፍነው በጉልበት ያዙት። "ያደረግነውን ለፖሊስ ብትጠቁም እንገድልሀለን!" ብለው በመዛት ሞባይል ስልኩን፣ ጃኬቱን፣ ጫማውን፣ ለማሳተም ጽፎ በሶፍት ኮፒ የያዘበትን ፍላሽ ነጥቀው በመውሰድ ተሰወሩ።

የአበባየሁ ተጨማሪ ትዕዛዝ

 ከጀርባ ባደረጉት ስምምነት መሰረት ግብረ አበሮቹ ከአበባየሁ ጋር ተገናኙ እና ድርጊቱን ለመፈፀም ያማከረው 2ኛው ግብረ አበር በዕቅዱ መሰረት ትእዛዙን መፈፀማቸውን በመግለፅ ፍላሹን ለአበባየሁ አስረከበው። አበባየሁም ለግብረ አበሮቹ "ሟች በህይወት እያለ በዚህ ጽሑፍ መጠቀም ስለማይቻል ዶክተር ቢንያምን መግደል አለባችሁ" አላቸው። የአበባየሁ ግብረ አበሮቹ በፊት መሪያቸው በ2ኛ ተከሳሽ በኩል ለግድያ ተጨማሪ ክፍያ እንደሚያስከፍሉ ገለፁለት። አበባየሁም ተስማማ።

በዚህም መሰረት ለግድያው ማስፈፀሚያ ለዋነኛ አማካሪ እና ሀሳቡን አፍላቂ 2ኛው ተከሳሽ ሠላሳ ሺ ብር፣ ለ4ኛ ተከሳሽ አስራ አምስት ሺ ብር፣ ለ5ኛ ተከሳሿ እና ለአጥማጇ ለሜሮን አምስት ሺ ብር፣ ለ3ኛው ተከሳሽ እና ክሱ ሲቀርብ ላልተያዘው አቡሽ ለተባሉት ተከሳሾች መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ተከፈላቸው።

ሜሮን ዶክተር ቢንያምን ድጋሚ አጠመደችው

 ዶክተር ቢንያም ሜሮን በዝርፊያው ድርጊት ውስጥ ያላትን ሚና አያውቅምና በአምስት ሺ ብር ተጨማሪ ክፍያ ልታስገድለው ወዳዘጋጀችው ወጥመድ በድጋሚ ሰተት ብሎ ገባ።

የውንብድና ዘረፋው ከተፈፀመበት ከሦስት ቀናት በኋላ ነሀሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም ሜሮን ስልክ ደውላ ዶክተር ቢንያምን ሻሸመኔ ከተማ ሻሌት ሆቴል ከምሽቱ 2:30 ገደማ እንዲመጣና እንዲገናኙ ቀጠረችው።

ዶክተር ቢንያም ቀጠሮውን አክብሮ ለ2ኛ ጊዜ ባለችው ሰዓት ተገኘ። ወደ ሆቴሉ ከመግባቱ በፊት ከሜሮን ውጭ ያሉት የአበባየሁ ግብረ አበሮች ከኋላው አፍነው በመኪናው ውስጥ በመወርወር እዚያው ሻሸመኔ ከተማ መልካ ኦዳ እና ለገጎቴ የሚባሉ ስፍራዎች ወሰዱት። አፉን እና እጅ እግሩን በፕላስቲክ አስረው በዘግናኝ ሁኔታ አሰቃዩት። በዚህም የተነሳ የጎድን አጥንቶቹ አድቅቀው፣ የግራ ሳንባ እና ኩላሊቶቹ ሰንጥቀው ነሐሴ 30 ቀን ገደሉት። አስክሬኑንም ወደ አርሲ ዳኮ ሆራ ቀሎ ቀበሌ ወስደው በመጣል ከሌሊቱ 5:30 ገደማ ሥራቸውን አጠናቀቁ።

ፖሊስ የወንጀሉን ፍፃሜ እና የተገኙ መረጃዎችን ተከትሎ ምርመራ አደረገ። ዐቃቤ ሕግ በምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስቱ ተከሳሾች ዶክተር ቢኒያም ማሞ ላይ በፈፀሙት የከባድ ውንብድና እና የከባድ ግድያ ወንጀሎች ክስ መሰረተ። ከአንድ ተከሳሽ በስተቀር ሌሎቹ ተይዘው በቁጥጥር ስል ውለው ክሳቸውን መከታተል ጀመሩ። አጥማጇ ሜሮን  ድርጊቱን በማመኗ የእድሜ ልክ እስር ተፈረደባት።

አበባየሁ ጥፋተኛ አይደለሁም የሚል ክርክር አቀረበ። ፍርድ ቤቱ አበባየሁን በተቀራራቢ ጊዜ ጥሩ ሥነምግባር ለሌላቸው በክሱ ላይ ከተ.ቁ.2-5 ለተከሰሱት ለወንጀል ግብረ አበሮቹ ትዕዛዝ በመስጠት እና በመፈፀም ከባድ ዝርፊያን እና ግድያ በመፈፀሙ ጥፋተኛ ነህ ሲል ወሰነበት። አበባየሁ ቤተሰብ አለኝና የቀደመ የጥፋት ሪከርድ የለብኝም ሲል ቅጣቱ እንዲቀነስለት  የቅጣት ማቅለያ አቀረበ።

ፍርድ ቤቱ ግን የቅጣት ማቅለያውን ያለፈ የህይወት ታሪኩ መልካም ነው ተብሎ በማቅለያነት ሊያዝ አይገባም ብሎ ስላልተቀበለው። በሞት ቅጣት እንዲቀጣ ወሰነ።

የአበባየሁ ይግባኝ

ከሜሮን በስተቀር የሌሎቹ አባሪዎቹ ቅጣት በውሳኔው ላይ ባይገለፅም አበባየሁ የሞት ቅጣት ውሳኔው ላይ በየደረጃው ይግባኝ አቅርቦ ስላልተሳካ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ላይ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ሲል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀረበ።

የሰበር አቤቱታው የቅሬታ ነጥቦችም ጥፋተኛ የተባለባቸው ሁለት ድርጊቶች ማለትም ከባድ ዝርፊያ እና ግድያ በአንድ የወንጀል ድንጋጌ የሚጠቃለሉ ናቸው፤ ማስረጃ እና ምስክሮች ባግባቡ አልተመረመሩም፤ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶቼን በመያዝ ቅጣቱ ሊቀልልኝ ሲገባ ባለማቅለሉ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉ ነበሩ። ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ጉዳዩን መርምሮ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በአበባየሁ ጉዳይ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ከማንበባችሁ በፊት እስቲ የተነሳውን ጉዳይ በሚመለከት የወንጀል ሕጉ ላይ ያላችሁን ግንዛቤ ለመመዘን የራሳችሁን ግምት በመልክት መስጫው ላይ አስቀምጡልን።

አበባየሁ ከፈፀመው ወንጀል አንፃር የሞት ቅጥት ይገባዋል?

የቀድሞ መልካም ሕይወቱ በቅጣት ማቅለያነት ሊያዝለት ይገባል ወይስ አይገባም!?

ሰበር ምን አለ?

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአበባየሁን የሰበር አቤቱታ እና ያስቀርባል በተባለበት የቀደመ መልካም ባህሪ የቅጣት ማቅለያነት ላይ ዐቃቤ ሕግ የሰጠውን መልስ መርምሮ የወንጀል ሕጉን አጠላይ ዓላማና ድንጋጌዎችን አብራርቷል።

ማብራሪያው እንደሚለው የወንጀል ሕጉ ግብ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ነው። ይህን የሚያደርገውም በመጀመሪያ ስለ ወንጀሎች እና ስለቅጣታቸው በማስጠንቀቅ ነው። ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ካልሆነ ደግሞ ወንጀል አድራጊዎቹን በመቅጣት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፅሙና ለሌሎችም ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፅሙ እርምጃዎች እንዲፈፀምባቸው በማድረግ ነው። የወንጀል ቅጣት አወሳሰንን በተመለከተም የወንጀለኛውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን፣ ያለፈ የህይወት ታሪኩን፣ ወንጀል ለማድረግ ያነሳሱትን ምክንያቶች፣ የወንጀል ሀሳቡን ዓላማ፣ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርቱን ደረጃ እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነት እና የአፈፃፀሙን ሁኔታዎች በማመዛዘን ነው። ፍርድ ቤቱም የወንጀል ሕጉን ልዩ ድንጋጌዎች ባገናዘበ መልኩ እጅግ ቀላል ከሚባለው እስከ መጨረሻው ከባድ ቅጣት መወሰን የሚችል ሲሆን፣ ይህም በትክክል እና በወጥነት እንዲተገበር የቅጣት አፈፃፀም መመሪያ ወጥቷል።

ዳኞች ቅጣትን ሲወስኑ የሚያመዛዝኗቸው በርካታ የአጥፊ ሁኔታዎች ቢኖሩም የቅጣት አወሳሰናቸው መሰረት የወንጀል አድራጊው ግላዊ የአደገኝነት መጠን መሆኑን የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 88(2) ድንጋጌ ይዘትና አቀራረፅ ያስረዳል።

የመምህራኑ የሟች የዶክተር ቢንያም እና የአስገዳይ የአበባየሁ ጉዳይ

የተያዘውን ጉዳይ በተመለከተ አበባየሁ ጥፋተኛ የተባለው በሁለት ግዙፍነት ባላቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ማለትም ከአምስት እስከ ሀያ አምስት ዓመት በሚያስቀጣው በከባድ የውንብድና ወንጀል እንዲሁም ዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት የሚያስቀጣውን ከባድ ግድያ በመፈፀም ነው።

እነኚህ ሁለት ወንጀሎች በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ላይ እርከን የወጣላቸው ሲሆን አበባየሁ(አመልካች) ሁለተኛውን ክስ ከባድ ውንብድናውን ከፈፀመ በኋላ የመጀመሪያውን ክስ ከባድ ግድያውን ያስፈፀመው ከሟች ዶክተር ቢንያም ማሞ የወሰደውን ጽሑፍ ለማሳተም እና የግሉን ስብዕና የማሳደግ ጥቅም ለማግኘት የሟች መገደል አስፈላጊ ነው በሚል አስነዋሪ የአፍቅሮተ ንዋይ ስሜት ነው። ውንብድናውና ግድያው የተፈፀመውም ከ2ኛ-5ኛ ተከሳሾች የነበሩትን የውንብድና ቡድን አባላት በመጠቀም በውንብድና ተግባር የወሰደውን ከሟች የዕውቀት ብርሃን የተገኘውን ጥበብ(ጽሑፍ) የአእምሮ ፈጠራ ውጤት እንዳይገለፅ ለማድረግ ነው። በመሆኑም የወንጀል ድርጊቱ ከባድነት እና አፈፃፀሙ ሲታይ ሁለተኛው ክስ በመጀመሪያው ክስ በሚያስቀጣው ዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት ስር የሚጠቃለል ነው።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ በውሳኔው መደምደሚያ ላይ "ሟች ዶክተር ቢንያም ማሞም ሆኑ ገዳይ አበባየሁ የሀገሪቱ ሀብት እና በዩንቨርስቲ መምህራንን የሚቀርፁ ባለሙያዎች ሆነው በመልካም ባህሪያቸው ለህብረተሰቡ አርአያ ተደርገው የሚወሰዱ ሆነው ሳለ ገዳይ ፍፁም ወራዳ የሆነ ተግባር መፈፀሙ አደገኛ ባህሪውን የሚያመላክት ነው። አበባየሁ (አመልካች) ያቀረበው የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመኖር የቅጣት ማቅለያ በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት ያላገኘውም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 117 አንፃር የድርጊቶቹ አፈፃፀም ከባድነት በተለይም የአመልካችን አደገኛነት መሰረት ያደረገ በመሆኑ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት አልተቻለም" ብሎ በመደምደም በዚህ ድምዳሜ ላይ ተመስርቶም የአበባየውን የሰበር አቤቱታ ባለመቀበል የስር ፍርድ ቤት ያሳለፈበትን የሞት ቅጣት ውሳኔ አፅንቶታል። ውሳኔውም በሰ.መ.ቁ.135787 መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተሰጠ ሲሆን በሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 22 ላይ ታትሞ ወጥቷል።

ኪዳኔ መካሻ የሕግ ባለሙያ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top