የ2016 ዓ.ም እንዴት አለፈ?

8 Days Ago 256
የ2016 ዓ.ም እንዴት አለፈ?

የ2016 ዓ.ም እንዴት አለፈ? ቀጥሎ ዋና ዋና ክስተቶችን እንመለከታለን

  1. መስከረም

አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ በሁሉም ደረጃዎች ወደ ሥራ የገባው በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው፡፡

ለፈተና ከተቀመጡት 845 ሺህ 188 ተማሪዎች መካከል 27 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡበት የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ውጤት ይፋ የሆነው በዚሁ በመስከረም ወር ነው።

  1. ጥቅምት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በቅርበት በሚትገኝበት የቀይ ባሕር ላይ መዳረሻ የማግኘት መብቷን የገለጹት በጥቅምት ወር ነበር፡፡ ቀይ ባሕር እና አባይ የኢትጰዮጵያን ህልውና የሚበይኑ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በነዚህ ሀብቶቿ ለመጠቀም ትብብርን ታስቀድማለች ነው ያሉት፡፡

ሰላም ሚንስቴር መንግሥት ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ላይ ያሏትን ብሔራዊ ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እንዲያረጋግጥ የሚጠይቅ ረቂቅ ሰነድ ያጋጀው በጥቅምት ወር ነው። ረቂቅ ሰነዱ፣ ኢትዮጵያ ወደብ ለመገንባት እና ለመጠቀም እንዲሁም በቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጠና መውጫ በር የማግኘት መብት እንዲኖራት የሚጠይቅ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳዑዲ-አፍሪካ ጉበኤ ላይ የተሳተፉት በጥቅምት ወር ነበር፡፡ ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌህ እና ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ መሐመድ ጋርም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረው ነበር፡፡

ለ2016/17 ዓ፣ም የምርት ዘመን በቀን ከ20 ሺህ ቶን በላይ ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ ከመርከብ መራገፍ የጀመረው በጥቅምት 2016 ዓ.ም ነው። የማዳበሪያ ግዢው ቀድሞ እንዲካሄድ የተደረገው በ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን ያጋጠመውን የማዳበሪያ በጊዜ አለመድረስ ችግር ለመቅረፍ ታስቦ ነው፡፡ በዚያም ምክንያት ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያው ቀድሞ በመድረሱ አርሶ አደሮች ያለችግር ማዳበሪያውን ሊያገኙ ችለዋል፡፡

  1. ዳር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በG20 Compact with Africa (CWA) ጉባኤ ላይ የተሳተፉት በኅዳር ወር ነበር፡፡ ከጉባኤው አስቀድሞም ከጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር የሀገራቱን የትብብር መስኮች ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከጉባኤው ጎን ለጎንም የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን አግኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይይ ሰፊ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦስትሪያ ቬና በተካሄደው 20ኛው የተባበሩት መንግሥታት ኢንደስትሪ ልማት ድርጅት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉባኤው የክብር እንግዳ በመሆን የእራት ግብዣ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ የጉባኤው ቁልፍ ንግግር አቅራቢም ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ በቼክ ሪፐብሊክ የሥራ ጉብኝት አድርገው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔትር ፊያላ ጋር በሁለቱ ሀገራት የልማት ትብብሮች የተወያዩትም በኅዳር ወር ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ተሞክሮዎቿን ያካፈለችው በኅዳር ወር በተካሄደው ኮፕ28 ላይ ነው፡፡

  1. ታኅሳስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ የባህር በር ስምምነት የተፈራረሙት በኅደር ወር ነበር፡፡ በሁለቱ ወገኖች የተፈረመው የጋራ የትብብር እና የአጋርነት መግባቢያ ሰነዱ ለኢትዮጵያ በሊዝ ኪራይ ወደብ እና ወታደራዊ ጦር ሠፈር 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ዳርቻ የምታገኝበት ነው።

ኢትዮጵያ ብሪክስን በይፋ የተቀላቀለችው በታኅሳስ ወር ነው፡፡ አምስት ሀገራት ያቋቋሙት ብሪክስ ተጨማሪ አምስት አዳዲስ አባላትን በመጨመር ወደ 10 አባላት አድጓል፡፡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ  ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ኢራን ብሪክስ በአባልነትን የተቀላቀሉት ሀገሮች ናቸው።

  1. ጥር

በዓይነትም በመጠንም ልዩ የሆነችው ግዙፏ የኢትዮጵያ መርከብ “ዓባይ ፪” ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ጭነት ይዛ ጅቡቲ ወደብ የደረሰችው በጥር ወር ነው፡፡ መርከቧ ቀደም ሲል በክራይ መርከቦች ሲከናወን የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ተግባርን ተወጥታለች፡፡

  1. የካቲት

የኢትዮጵያውያን የነጻነት ቀንዲል የሆነው የአድዋ መታሰቢያ የተመረቀው በየካቲት ወር ነው፡፡ መታሰቢያው የአድዋን ታሪክ በአንድ አሰባስቦ ለትውልድ የሚያስተላልፍበት ሙዚየም የተገነባለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ባንክን ጨምሮ በ15 ዘርፎች ፍቃድ መስጠት የጀመረው በየካቲት ወር ነው፡፡ ባለሥልጣኑ የተዘበራረቀውን የኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያን መስመር ለማስያዝ ብሎ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣ ሰፊ ዝግጅቶችን አድርጎ ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ ባለሥልጣኑ ፍቃድ የወሰዱትን አካላትን ይቆጣጠራል።

"ሀገሬን አትንኳት፣ ውብ አዲስ አበባ፣ ሳይሽ እሳሳለሁ፣ ክፈቺውና መስኮቱን፣ የከረመ ፍቅር፣ ትዝ ባለኝ ጊዜ" በሚሉት እና በሌሎች ተወዳጅ ዘፈኖቹ የሚታወቀው አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በየካቲት ወር ነው።

  1. መጋቢት

መጋቢት 2010 ዓ.ም በመጣው ለውጥ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተካሄደው በመጋቢት ወር ነው፡፡ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ከሽግግሩ በኋላ የተገኙ ድሎችንና ሁለንተናዊ ለውጦች ተጠቃሚ መሆናቸውን እና ወሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመትን መሆኑ ድርብ ድል እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ 

ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ጭማሪን ለመከላከል የተዘጋጀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው በመጋቢት ወር ነው። አዋጁ ሲፀድቅ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑ ተጠቅሶ፣ በተከራይ እና አከራይ መካከል ስለሚኖረው ውል፣ የውሉን ተፈፃሚነት የሚቆጣጠር አካል ይኖረዋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ“ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን መርቀው የከፈቱት በመጋቢት ወር ነው፡፡ ማዕከሉ በችግር ላይ ለሚገኙ ሴቶች አዲስ የህይወት ምዕራፍ የሚከፍት ነው። የሴቶችን እኩልነት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና እንዳለው ነው በምረቃው ወቅት የተገለጸው።

  1. ሚያዚያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ሱዝማን እና ቡድናቸውን የተቀበሉት በሚያዚያ ወር ነው፡፡ የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በግብርና፣ ጤና፣ ሥርዓተ ምግብ፣ አካታች ፋይናንስ እና ሌሎች ዘርፎች የሚሰጠው ጠቃሚ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ዕድገት ከፍ ያለ አስተዋጽ እንዳለው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስታወቁት፡፡ ሚስተር ቢል ጌትስ ባለፈው ሳምንትም የዚሁ አካል የሆነ ጉብኝት በኢትዮጵያ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጽዱ፣ ምቹና ውብ አካባቢን መፍጠርን ዓለማ ያደረገውን የ"ጽዱ ጎዳና-ኑሮ በጤና" ንቅናቄ ያስጀመሩት በሚያዚያ ወር ነው፡፡ ንቅናቄውን በርካታ ተቋማት እና ግለሰቦች ተቀላቅለው የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

የ‘ስታርት አፕ’ ዐውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው በመጋቢት ወር ነው፡፡ ዐውደ ርዕዩ በዘርፉ ያሉ ተሳታፊዎችን የፈጠራ ምናብ ስፋት ማሳያ እንደሚሆን ነው የተገለፀው፡፡

የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት ስሚ መድረክ የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካለኝ(ዶ/ር) በተገኙበት የተጀመረው በመጋቢት ወር ነው፡፡ የ2017 የበጀት ዝግጅት ዓላማ የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው በ2016-2ዐ18 የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ማስፈጸም እና የመንግስትን ፈጣን፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ የዕድገት ፖሊሲን ማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  1. ግንቦት

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተመራው ልዑካን ቡድን የአፍሪካ-ኮሪያ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉት በግንቦት ወር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጉበኤው ገን ለጎን ከኮሪያ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡ ኮሪያ እና ኢትዮጵያም የአንድ ቢሊዮን ዶላር የብድር እና ድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 24ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ያከበረው በግንቦት ወር ነው፡፡ የምሥረታ በዓሉ በፓናል ውይይት፣ በመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ እና በተለያዩ ዝግጅቶች ነበር የተከበረው፡፡

በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ የተገነባው ታላቁ የአባይ ወንዝ ድልድይ የተመረቀው በግንቦት ወር በው፡፡ ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የቀድሞው ድልድይ እድሜ ጠገብ ከመኾኑም በላይ ዘመኑን የዋጀ፣ ፈጣን እና ተደራሽ የኾነ የሕዝብ ትራንስፖርት በመስጠት በኩል ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅን ሲፈጥር የቆየ ነበር፡፡ ይህን ችግር የሚፈታው እና ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የተገነባው አዲሱ ድልድይ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ አካል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

  1. ሰኔ

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ የምክክር መድረክ ያካሄደው በሰኔ ወር ነው፡፡ በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስዳድር እንዳሻው ጣሰው፣ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር)፣ ሚኒስትሮች፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አመራሮች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላጥ ሚኒስትሩ ህገወጥ ፍልሰትንና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የገቡት በሰኔ ወር ነው።እነዚህ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በታኅሳስ ወር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

  1. ሐምሌ

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሙሉ ትግበራ ይፋ የተደረገው የተደረገው በሐምሌ ወር ነው። ማሻሻያው የዕዳ ጫና፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ዝቅተኛ የዘርፎች ምርታማነት፣ ዝቅተኛ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና የሀብት ብክነት፤ የተረከባቸው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕዳዎችን ለማሻሻል የወጣ ነው።

የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ መመዝገቢያ ይፋ የሆነው በሐምሌ ወር ነው፡፡

  1. ነሐሴ

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአንድ ጀምበር 615.7 ሚሊዮን ችግኞች የተተከሉት በነሐሴ ወር ነው፡፡ በዘንድሮው አምስተኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፉት አምስት ዓመታት አጠቃላይ የተተከሉ ችግኞችን ቁጥር 40 ሚሊዮን ለማድረስ እየተወራ ይገኛል፡፡ የዚህን ዓመት አረንጓዴ አሻራ ልዩ የሚያደርገው ያለፉት ስኬቶች እና ክፍተቶች ተገምግመው ወደ ሥራ መገባቱ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ የተሳተፉት በነሐሴ ወር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከቻይና መንግሥት ኃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረገው ውይይትም በ17 ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ተፈርሟል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top