በቼክ መክፈል ብድርን ያስረዳል?

17 Days Ago 1109
በቼክ መክፈል ብድርን ያስረዳል?

ያልተከፈለው ብድር

አቶ ጌታቸው ለአቶ ተሾመ በ2006 ዓ.ም "አንድ መቶ ሺህ ብር አበድሬው አልከፈለኝም፤ ስለዚህ ይክፈለኝ" ሲሉ ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቀረቡ፡፡

ማስረጃዬ ያሉትም ለአቶ ተሾመ በ2006 ዓ.ም ፅፈው የሰጧቸውን እና ግለሰቡም በወቅቱ ባንክ ቀርበው የመነዘሩት የአንድ መቶ ሺህ ብር ቼክ ነበር፡፡

ተከሳሹ አቶ ተሾመም ለፍርድ ቤቱ በሰጡት መልስ "ብር አልተበደርኩም፤ ቼኩን ከሳሽ የሰጠኝም ከዚህ ቀደም ሰጥቼው የነበረውን ገንዘብ ለመክፈል ነው፡፡ ከሳሼም እኔን ለመክሰስ የሚያስችል መብት እንዳለው የሚያሳይ ማሰረጃ አላቀረበም፤ ስለዚህ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ" ሲሉ መልስ ሰጡ፡፡

ፍርድ ቤቱም ክርክሩን መርምሮ ከሳሽ ብድሩን ስለማበደሩ በሕጉ አግባብ ባለማስረዳቱ፣ ክሱ ተቀባይነት የለውም ሲል ለተከሳሽ ፈረደለት፡፡

ከሳሽ በውሳኔው ቅር ተሰኝቶ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቀረበ፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ይግባኙን መርምሮ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አፀናው። የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም ውሳኔውን አይነቀፍም ሲል አጸናው፡፡

ሦስቴ የተረቱት ከሳሽ አቶ ጌታቸውም የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረም ሲሉ የመጨረሻ ስልጣን ላለው ለፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤት አሉ፡፡የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ምን ሚሆን ይመስላችኋል? ውሳኔውን ከማንበባችሁ በፊት ግምታችሁን በአስተያየት መስጫው ውስጥ አጋሩን።

ሰበር ምን አለ?

የፌደራሉ ሰበርም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሰረት መብት አለኝ የሚለው ከሳሽ የሚጠይቀውን መብት ማስረዳት አለበት፤ ከሳሹ ብድሩ መኖሩን አግባብነት ባለው ማስረጃ ካስረዳ ተከሳሹ ደግሞ እራሱን ከኃላፊነት ለማዳን የመከላከያ ማስረጃ የማቀረብ ሸክም ወይም ኃላፊነት አለበት፡፡

ከሳሹ ያቀረበው ማስረጃ ግን ቼክ ነው፡፡ ቼክ ደግሞ በንግድ ሕጉ መሰረት ሀተታ የሌለበት የክፍያ ወይም የገንዘብ ሰነድ እንጂ ብድር መኖሩን የሚያስረዳ ሰነድ አይደለም፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2472(1) መሰረት ከ500 ብር በላይ የገንዘብ ብድርን ማስረዳት የሚቻለው በፅሁፍ በተደረገ የብድር ውል ወይም በፍርድ ቤት በተደረገ የመሀላ ቃል ተበዳሪው መበደሩን ሲያምን ብቻ ነው፡፡

ከሳሹ ግን ያቀረቡት ማስረጃ ቼክ በመሆኑ፣ ቼክ መስጠታቸው ደግሞ ገንዘቡን በብድር ለተከሳሹ እንደሰጡ ስለማያስረዳ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም ብሎ አፅንቶታል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰበር መ.ቁ 123984 ሚያዝያ 25 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ ቅፅ 21 የሰበር ውሳኔዎች መጽሐፍ ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ ሲጠቃለልም ብድር ከብር 500 በላይ ከሆነ በጽሑፍ የብድር ውል በማቅረብ ወይም ተበዳሪው ፍርድ ቤት ቀርቦ ካላመነ በሌላ መንገድ ማስረዳት አይቻልም። ቼክ ቼክ ነው። የክፍያ መፈፀሚያ መንገድ ነው። ቼክም ሆኑ ሌሎች ዘመናዊ የክፍያ መንገዶች የሞባይል ወይም የባንክ ገንዘብ ገቢ የተደረገበት ደረሰኝ ብቻውን ብድር መኖሩን አያስረዳም።

ክፍያ መፈፀሚያ መንገዶች የግድ ብድር መኖሩን አያሳዩም። ቢያንስ የክፍያ መግለጫ ሚለው ላይ ብድር መሆኑን መግለፅ ምናልባት ክርክር ቢነሳ የብድር ግንኙነት መኖሩን ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ ይልቅ ስንበደርም ሆነ ስናበድር ቢያንስ ሁለት ምስክሮች በፈረሙበት የጽሑፍ ውል ማድረጉ ገንዘቡ አልመለስ ሲል በሕግ ለማስመለስ ያስችላልና ሕጉ የሚለንንን ማድረጉ ይመከራል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top