ስመጥሩ የተሽከርካሪ አምራች ጃክ ሞተርስ በኢትዮጵያ የኤክትሪክ ተሽከርካሪ ለመገጣጠም መወሰኑን አስታወቀ

1 Mon Ago 366
ስመጥሩ የተሽከርካሪ አምራች ጃክ ሞተርስ በኢትዮጵያ የኤክትሪክ ተሽከርካሪ ለመገጣጠም መወሰኑን አስታወቀ

ስመጥሩ የቻይና ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጃክ ሞተርስ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም ሥራ ለመጀመር መወሰኑን የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ዛንግ ሆርኖግ ገለፁ፡፡

የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ይህን የገለፁት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከጃክ ሞተርስ ፕሬዚዳንት እና ሃዩጃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

ሚኒስትሩ በውይይት ወቅት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማምረትና መገጣጠም ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምቹ የፖሊሲ እና ገበያ ሁኔታዎች ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

ጃክ ሞተርስ እና ሃዩጃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠም ባሻገር የኤልክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅን በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ማምረት የሚችልባቸው ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

አክለውም በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በኩል ጃክ ሞተርስ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገባ ለማስቻል አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የጃክ ሞተርስ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኝበት የለውጥ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተቋማት ምቹና አስተማማኝ የገበያ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልፀው፤ ድርጅታቸው በዚሁ ምቹ ሁኔታ በመሳብ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ  ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ መወሰኑን ገልጸዋል።

ድርጅታቸው ባጠረ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ያሰበውን የኤሌትሪክ ተሽከርካሮዎች መገጣጠም ስራም እንደሚጀምር ያላቸውን ዕምነት መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ጃክ ሞተርስ መቀመጫውን ቻይና በማድረግ በተሽከርካሪዎች ምርትና መገጣጠም ዘርፍ ላይ የተሰማራ ስመጥር ዓለም አቀፍ አምራች ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top