በመቐለ ከተማ በ2.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

1 Mon Ago 569
በመቐለ ከተማ በ2.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

በመቐለ ከተማ በሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የአስፋልት መንገዶችና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ የልማት ፕሮጀክቶቹን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በስነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ዛሬ ለምረቃ የበቁት የመንገድና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የውስጥ አቅምን ተጠቅሞ ጥራታቸውን የጠበቁ የልማት ሥራዎችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ናቸው።

ከህዝብ ጋር በተቀናጀ መንገድ ከተሰራ ሁሉንም ነገር ማከናወንና ማሳካት ይቻላል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ፕሮጀክቶቹ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ህዝብን በማሳተፍ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።

የመቐለ ከተማ ከንቲባ አቶ ይትባረክ አማሃ በበኩላቸው፤ በከተማው ለተገነባው የአንድ ኪሎ ሜትር ዋና የአስፋልት መንገድ እና ተጓዳኝ የልማት ሥራዎች ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

የአስፋልት መንገዱን ተከትሎ የውሃ ቧንቧ፣ የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ እና የቴሌኮም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ከንቲባው አመልክተዋል።

ከፕሮጀክቶቹ ምረቃ በተጨማሪ በ35 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የአሸንዳ አደባባይ በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታ ለማካሄድ የመሰረት ድንጋይ በአቶ ጌታቸው ረዳ መቀመጡን ኢዜአ ዘግቧል።

አደባባዩ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክትን ጨምሮ የተለያዩ የህዝብ መዝናኛዎች፣ የተለያዩ በዓላት ማክበሪያ ስፍራ፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የመኪና ማቆሚያ መሰል ፕሮጀክቶችን የሚያካትት ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top