የኢትዮጵያ ምርቶች በህንድ ያላቸውን ገበያ ለማሳደግ ይሰራል፡- በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር

28 Days Ago 221
የኢትዮጵያ ምርቶች በህንድ ያላቸውን ገበያ ለማሳደግ ይሰራል፡- በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር

የኢትዮጵያ ምርቶች በህንድ ያላቸውን ገበያ ለማሳደግ የህንድ ኤምባሲ እንደሚሠራ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለጹ።

በአዲስ አበባ በህንድ ኤምባሲ አዘጋጅነት በተካሄደ መድረክ፤ ኢትዮጵያ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች፣ ጥጥ፣ የከበሩ ማዕድናት እና የቡና ምርቶች ወደ ህንድ ገበያ በስፋት ልትልክ በምትችልባቸው ዕድሎች ዙሪያ በተደረገ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ውይይት ተደርጓል። 

በፈንጆቹ 2022 ኢትዮጵያ እና ህንድ የነበራቸው የንግድ ልውውጥ 2.8 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተጠቅሷል።

ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ 80 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ወደ ህንድ ገበያ የምትልካቸውን ምርቶች ማሳደግ ላይ መሥራት እንደሚገባት ተመላክቷል።

በጥናቱ ኢትዮጵያ ወደ ህንድ ገበያ የምትልካቸውን የምርቶች ብዛት በማሳደግ የንግድ ሚዛኑን ማጥበብ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

እንደ ቡና ያሉ ምርቶችን በመላክ የህንድን የገበያ አማራጭ መጠቀም እንደሚገባም በመድረኩ የተመላከተ ሲሆን፤ ህንድ ሰፊ የሆነ የግብርና ምርቶች ተጠቃሚ ያላት ሀገር መሆኗ ለኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ምቹ አጋጣሚ ነው ተብሏል። 

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ህንድ የኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷን ለማሳደግ እና ለማስፋት እየሠራች መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በህንድ ያለውን የገበያ እድል በአግባቡ በመጠቀም የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ጥናትም የንግድ ትስስሩን እንደሚያጠናክረው አንስተዋል።

በአባዲ ወይናይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top