1 ሺህ 499ኛው የነብዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል ነገ ይከበራል

4 Days Ago 1301
1 ሺህ 499ኛው የነብዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል ነገ ይከበራል

1 ሺህ 499ኛው የነብዩ መሀመድ ልደት (መውሊድ) በዓል ነገ መስከረም 5 ቀን 2017 ዓ. ም እንደሚከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ በዓሉን ዝግጅትና አከባበር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መገለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የመውሊድ በዓል አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸይኽ አብዱልሐሚድ አህመድ እንደገለጹት፤ ክብረ በዓሉ በትውፊቱ መሠረት በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች “የሰላሙ ነብይ” በሚል መሪ ሃሳብ  በታላቁ አንዋር መስጊድ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።

በዕለቱም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶች ይከበራል ብለዋል።

የእስልምና ኃይማኖት ለሰላም የሚሰጠውን ትኩረት ትልቅ መሆኑን ገልጸው፣ሕዝቦች ልዩነታቸውን አቻችለው በሰላም በመኖር የነብዩን ፈለግ መከተል አለባቸው ብለዋል።

በዓሉ ''የሰላሙ ነብይ'' በሚል መሪ ሃሳብ መከበሩ ሰላም ያለውን ከፍተኛ ዋጋ ለማሳየት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዕለቱ የነብዩ መሀመድ ታሪክ፣ የእስልምና አመጣጥና ሀዲሶች  የሚነበቡ ሲሆን የኃይማኖት አባቶች፣ ኡለማዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

 

ሕዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር ያለምንም ልዩነት በመረዳዳት፣ በሰላም፣ ፍቅርና በመቻቻል ሊሆን እንደሚገባም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም የተቸገረ ወገናቸውን በመርዳት፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህልን በሚያጠናክሩ መልኩ በዓሉን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top