አዲስ ዓመት እና እቅድ

4 Days Ago 145
አዲስ ዓመት እና እቅድ

የሰው ልጅ በሕይወት ሲኖር ጊዜን በቀናት፣ በወራትና በዓመታት ከፋፍሎ እንደመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ አዲስ ዓመት ሲመጣ ማቀድ፣ አዲስ ተስፋን መሰነቅ የተለመደ ነው፡፡

በአዲሱ ዓመት ሱስ አቆማለሁ፣ ስፖርት መስራት እጀምራለሁ፣ አመጋገቤን አስተካክላለሁ የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ መልካም የጤና እቅዶች የሚታቀድበት ነው፡፡

ይህን በሚመለከት ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ ያደረጉት የስነልቦና ባለሞያ አቶ ናሁሰናይ ፀዳሉ፤ የወቅቶች መለዋወጥ እና የአዲስ ዓመት መምጣት የሰው ልጅ የኑሮና የአስተሳሰብ ሁኔታ ላይ በእጅጉ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለዋል።

በተለይ በሀገራችን የክረምቱ የዝናብና የብርድ ጊዜ አልፎ የበጋው ፀሀይ ወደሚፈካበት ወቅት ስንሻገር ሁሉም ሰው በሀሳቡ ከተቻለም በጽሑፍ እቅዱን የማስፈር ልምድ እንዳለው ባለሞያው ያስረዳሉ።

አንድ የአእምሮ ጤናው የተጠበቀ ሰው ዘወትር ራሱን ለማሳደግና በውስጡ ያሉ መልካም ያልሆኑ ስሜቶችንና ባህሪዎችን የመቀነስ እንዲሁም የሚጎዱ ልምምዶቹን የማስወገድ ከፍተኛ ፍላጎት እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ዓመት አልፎ አመት ሲተካም ይህ ሰው በአቅሙና በፍላጎቱ መጠን ሊያሳካው የሚፈልገው እቅድ በውስጡ ያመነጫል ነው ያሉት ባለሙያው።

እነዚህ እቅዶች የሚመነጩት በአብዛኛው በሁለንተናዊ መልኩ እራስን ለማሻሻልና ለማሳደግ ካለ ውስጣዊ ፍላጎት የተነሳ ነው የሚሉት የስነ-ልቦና ባለሞያው፤ የእቅዱም መሠረት በሚመጣው ዓመት ላይ ካለ ብሩህ ተስፋ የመነጨ እንደሆነ አንስተዋል።

በተጨማሪም ካሳለፍነው ዓመት ውድቀቶቻችንና ድክመቶቻችን በመማር እንደሚመነጭም ባለሞያው አመላክተዋል።

ማቀድ የስነ አእምሮ ጤናው የተጠበቀ ሰው ባህሪ እንደሆነ የሚገልጹት የስነ-ልቦና ባለሞያው፤ በተጨማሪም እቅድን አቅዶ በተግባር መፈጸመ በራስ መተማመንን፣ መነቃቃትን እና ተግባቦትን ስለሚያሳድግ ለስነልቦና ጤናችን መልካም ልምምድ  እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

ለአዲስ አመት ጥሩ እቅዶች ማስቀመጣችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከማድረጉም ባለፈ ውጥረትን እንደሚያስወግድ የሚያነሱት ባለሙያው፤ እቅዱን ባንፈፅም ማቀዳችን ብቻ ከውስጥ ወቀሳና ሊሰማን ከሚችል ድባቴ በመጠኑም ቢሆን እንድናለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከእቅዳችን የተነሳ በአዲሱ ዓመት ብሩህ እሳቤና ተስፋን እናጎለብታለን፣ ዓመቱን በብርታት እንድንጀምርም ይረዳናል ብለዋል የስነ-ልቦና ባለሞያው አቶ ናሁሰናይ ፀዳሉ፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top