ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የመሩት የብሪክስ የደኅንነት ስብሰባ በሩሲያ ተካሄደ

26 Days Ago 305
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የመሩት የብሪክስ የደኅንነት ስብሰባ በሩሲያ ተካሄደ

በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መሪነት የብሪክስ አባል ሀገራት ከፍተኛ ተወካዮች የተሳተፉበትና ትኩረቱን የደህንነት ጉዳዮች ላይ ያደረገ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡

በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በቆስጠንጢኖስ ቤተ መንግስት በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ኢትዮጵያም ተሳታፊ ሆናለች፡፡

በመድረኩ ላይ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው በዚህ ሕንፃ ውስጥ የብሪክስ ጥምረት የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፤ ጥምረቱ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ መምጣቱን ገልፀዋል።

የብሪክስ የደኅንነት ስብሰባ በዚህ መልኩ ሲካሄድ ለ14ኛ ጊዜ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ስብሰባ ጥምረቱን ከጥር 1 2024 ጀምሮ የተቀላቀሉ የሀገራት ተወካዮች የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የመድረኩ መካሄድ በመጪው የጥቅምት ወር በሩሲያ ካዛን ሊካሄድ ለታቀደው የብሪክስ አባል ሀገራት የከፍተኛ ተወካዮች ስብሰባ ዝግጅት ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በመጪው ጥቅምት ወር በሚደረገው የብሪክስ ስብሰባ በጥምረቱ አባል ሀገራት መካከል ስላለው ሁለንተናዊ ትብብር ጥልቅ ምክክር እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡

በመድረኩ በተለያዩ ዘርፎች እና የትብብር መስኮች ላይ የሚያተኩሩ የስምምነት ፓኬጆችን በአባል ሀገራቱ መካከል ለመፈራረም እቅድ መቀመጡንም መግለፃቸውን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

በመድረኩ የዓለምን የደኅንነት ምህዳር ጽንፈኝነት፣ ግጭቶች፣ ሽብርተኝነት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ፈተናዎች እየተፈተኑ መሆኑ ተገልጿል።

የስብስባው ተሳታፊዎች የብሪክስ አባል ሀገራት የደኅንነትና የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከትናትን ጀምሮ በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ የደኅንነት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የተሳተፈች ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመሩት መድረክ ላይ መካፈል ችላለች፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top