ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ወንዞችን በማጽዳት ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ በስፋት ተሰርቷል፦ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ

3 Mons Ago 816
ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ወንዞችን በማጽዳት ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ በስፋት  ተሰርቷል፦ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ

ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ ያሉትን ወንዞች የማጽዳት እና ለአከባቢው ነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ በስፋት መሰራቱን የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ይመኙሻል ታደሰ  ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የተፋሰስ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት  እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በኮሪደር ልማቱ ብቻ 8 የሚሆኑ ወንዞች እንደፀዱ እና አከባቢው ላይ ፓርክ፣ የህዝብ መናፈሻ፣ የልጆች መጫወቻ፣ መቀመጫዎች መገንባታቸውን ኃላፊዋ አንስተዋል፡፡

ለአብነት የአቡዋሬ እና የቀበና ወንዝን የማጽዳት ስራዎች እንደተከናወኑ ጠቁመዋል፡፡

በ 5ቱም የኮሪደር ልማት ስራ ላይ ወደ 57.8 ሄክታር የሚሆን አረንጓዴ ልማት መሰራቱን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ ከ40 በላይ የሚሆን የውሀ ልማት ፏፏቴዎች መከናወናቸውንም ገልፀዋል፡፡

የሚገነቡት ልማቶች የኦሎምፒክ ስታንዳርድ የሆኑ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የአንፊ ቲአትሮች  እንዲሁም ህብረተሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት፣ የእግር ጉዞ የሚሄድበት ቦታዎች ጭምር እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በላይኛው ተፋሰስ የሚገኙ የጉለሌ፣ የካ አና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በልዩ ትኩረት የተፋሰስ ስራዎች እንደሚሰራባቸው ያነሱት ኃላፊዋ፤ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ብቻ ከ476 ሄክታር በላይ የተፋሰስ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

የተፋሰስ ስራው የጎርፍ አደጋን ከመከላከል ባለፈ አከባቢው ላይ ያሉ የተተከሉ ችግኞችን ለመጠበቅ አንደሚያስችል አንስተዋል፡፡

ወንዞች ከመበከላቸው የተነሳ ለጤና እንዲሁም ለጓሮ አትክልቶች ጠንቅ የነበሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረም አንስተዋል፡፡

እዚህ አከባቢ ላይ ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች ምትክ ቦታ በመስጠት ስፍራው በተሻለ ሁኔታ እንዲለማ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ስለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡

ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የገቡት የእንጦጦ እና ወዳጅነት ፓርክ መናፈሻዎችን ተከትለው ያሉ ወንዞችን እንዲጸዱ በማድረግ ክፍት ቦታዎችን መልሶ ለህብረተሰቡ ለአገልግሎት መዋላቸውን አንስተዋል፡፡

በሁለተኛ ዙር በተፋሰስ እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ ላይ ያተኮሩ ከቻይና፣ ኮሪያ እና ከጣሊያን መንግስት ጋር በትብብር እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል፡፡

በሜሮን ንብረት   


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top