በረራ የሚከለከልበት፣ የዞዲያክ ምልክት የሚሰጥበት እስከ ሰባቱ ምሳሌዎች የአዲስ ዓመት አከባበር

4 Mons Ago 1018
በረራ የሚከለከልበት፣ የዞዲያክ ምልክት የሚሰጥበት እስከ ሰባቱ ምሳሌዎች የአዲስ ዓመት አከባበር

የዘመን መለወጫ በዓል በበርካታ ሀገሮች የሚከበርባቸው ባህሎች የተለያዩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ ባህል እና ሕዝባዊ መስተጋብር አለው፡፡ በዚህም መሰረት ነው ሀገራት አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩት፡፡ አዲስ ዓመት አብዛኛውን ጊዜ የአካባቢውን ባህል እና እምነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ይከበራል። አዲስ ዓመት በተለያዩ ሀገራት ባህል የተለየዩ አከባበሮች ቢኖሩትም ሁሉንም አንድ የሚያደርገው ግን አሮጌ ዘመን አልፎ አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ እንደሚቀበሉ ማመናቸው ነው፡፡

የጎርጎሮሳውያንን ዘመን ቀመር ከሚከተሉ ሀገራት የተለየ የአዲስ ዓመት አከባበር ካላቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ቀመር የፀሐይ እና የጨረቃ ዑደቶችን በመጠቀም የሚሠራ ነው፡፡ የወቅቶች ለውጥን ተከትሎ የሚከበረው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በጨለማ የሚመሰለው ክረምት መውጫ ላይ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በከባድ ዝናብ እና ደመና የታጀበው ክረምት አልፎ ሰማዩ የሚጠራበት፣ መስኮቹ በአበቦች የሚያጌጡበት መስከረም ለኢትዮጵያውያን የወቅት ለውጥ ብቻ ሳይሆን ትልቅ መንፈስ ማንቂያ ነው፡፡ ሰማዩ እንደ ጠራው እና ምድር በአበቦች እንደምታጌጠው ኢትዮጵያውያንም ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው ነው አዲስ ዓመትን በተስፋ የሚቀበሉት፡፡ 

ቀጥሎ በአጭር በአጭሩ የምንመለከታቸው ሀገራት እንዳንዳቸው የዘመን መለወጫ በዓላት ዓለም በስፋት ከሚያውቃቸው የአዲስ ዓመት አከባበሮች በጣም የተለዩ ናቸው፡፡

  1. የቻይና አዲስ ዓመት (የጨረቃ አዲስ ዓመት) – የቻይና አዲስ ዓመት በጨረቃ ዑደት መሠረት ከጥር መገባደጃ እስከ የካቲት አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ ይከበራል። በአከባበሩ የዘንዶ እና የአንበሳ ትርዒቶች፣ ርችቶች፣ የቤተሰብ መገናኘት፣ ለመልካም ዕድል መግለጫ ቀይ ጌጦች እና ገንዘብ ያለበት ቀይ ፖስታዎች ("hongbao") ይሰጣል፡፡ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አይጥ፣ በሬ፣ ነብር፣ ጥንቸል፣ ዘንዶ፣ እባብ፣ ፈረስ፣ ፍየል፣ ጦጣ፣ አውራ ዶሮ፣ ውሻ እና አሳማ ባሉት 12ቱ የዞዲያክ እንስሳት መካከል በአንዱ ይሰየማል
  2. ኖውሩስ (የፋርስ አዲስ ዓመት) – ኢራን እና ሌሎች የፋርስ አካባቢ ላሉት ሀገራት መጋቢት 21 አካባቢ የሚብተው የጸደይ ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ቀናቸው ነው። አከባበሩ ለ13 ቀናት ያህል የሚቆይ ሲሆን፣ "ሃፍት-ሲን" በመባል በሚታወቅ እና ተምሳሌታዊነት ያላቸው ሰባት ነገሮችን በጠረጴዛ ላይ በመደርደር በሚደረግ ዝግጅት፣ በእሳት ላይ በመዝለል እና የቤተሰብ አባላትን መጎብኘትን ያካተተ ነው። ይህ ዓይነቱ የአዲስ ዓመት አከባበር በኢራን፣ በመካከለኛው እስያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በፋርስ ሀገሮች ውስጥ ትልቅ የባሕል ክንውን እንደሆነ ይታወቃል።
  1. ሮሽ ሃሻናህ (የአይሁዳውያን አዲስ ዓመት) – በዕብራይስጥ የቀን አቆጣጠር መሠረት በመስከረም ወይም በጥቅምት ወር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚከበር ነው። ወደ ዮም ኪፑር (የስርየት ቀን) የሚያመራ የፀሎት፣ የጽሞና እና የንስሐ ጊዜ ነው። "ሾፋር" የሚሉት የአውራ በግ ቀንድን መያዝ፣ ለአዲስ ዓመት ጣፋጭነት ተምሳሌት የሆነውን ማርን በፖም መብላት፣ እንዲሁም በምኩራቦቻቸው በመገኘት በፀሎት ያከብራሉ።
  2. ሶንጋከራን (የታይላንድ አዲስ ዓመት) – ከሚያዚያ 5 እስከ 7 የሚከበር ሲሆን፣ የታይ ባህላዊ አዲስ ዓመት በመባል ይታወቃል፡፡ በመላው ሀገሪቱ በሚደረገው የውኃ መራጨት ባህላዊ አከባበሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ የውኃ መራጨት ውኃ ንጹህና መታደስን ለማመልከት ይጠቀሙበታል። በተጨማሪም ቤተ መቅደሶችን መጎብኘት፣ መልካም ማድረግ እና ባሕላዊ ጭፈራዎችን ያካትታል
  3. ዲዋሊ (በተወሰኑ የሕንድ ክልሎች የሚከበር አዲስ ዓመት) – እነዚህ የሕንድ ክልሎች አዲስ ዓመታቸውን በጥቅምት ወይም በኅዳር ወር የሚያከብሩ ሲሆን፣ ስያሜውም የመብራት በዓል በመባልም ይታወቃል። ለአንዳንድ ማህበረሰቦች (በተለይ በሰሜን) "ዲዋሊ" በሂንዱ ዘመን አቆጣጠር አዲስ ዓመት መጀመርያ ነው። የዘይት መብራት፣ ርችቶች ፣ የቤተሰብ መሰባሰብ፣ ድግሶች እና ስጦታ መለዋወጥን የበዓሉ አከባበር አካላት ናቸው።
  4. ናይፒ የኢንዶኔዥያ ዓዲስ ዓመት "የዝምታ ቀን" በመባል የሚታወቀው ይህ የኢነዶኑዢያውያን አዲስ ዓመት በመጋቢት ወር ይከበራል። በበዓሉ ዕለት በኢንዶኒዢያዋ ባሊ ደሴት ምንም የአውሮፕላን በረራ አይኖርም፤ ተሽከርካሪዎችም አይንቀሳቀሱም እንዲሁም ማንኛውም ሥራ ይዘጋል፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን ሰብስበው ስለ ራሳቸው ለማሰላሰል በየቤታቸው ይቆያሉ። ከናይፒ አንድ ቀን በፊት ክፉ መናፍስትን ያባርራል ብለው የሚያምኑበትን "ኦጎ-ኦጎህ" የተባለውን ምስል ይዘው ጉዞ ያደርጋሉ።
  5. "ቴት" የቬትናም የጨረቃ አዲስ ዓመት፡- አብዛኛውን ጊዜ በጥር ወር መገባደጃ ወይም በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ከቻይናውያን አዲስ ዓመት ጋር ይከበራል። አከባበሩ የቤተሰብ መገናኘትን፣ ቤቶችን ማጽዳትን፣ ልዩ ልዩ ምግቦችን ማዘጋጀትን፣ የዘመዶቻቸውን መቃብሮች መጎብኘትን እና የዕድል መክፈቻ ነው ተብሎ የሚታመነውን "li xi" የሚባል የገንዘብ ስጦታ መስጠትን ያካትታል፡፡ ትርዒቶችን፣ የአንበሳ ጭፈራዎችን እና ርችቶችንም ያካትታል።
  6. ሆግማኔ – ስኮትላንድ፡- እ.ኤ.አ ታህሳስ 31 ቀን የሚከበረው የስኮትላንድ አዲስ ዓመት ዋዜማ በዓል ነው። በመጀመሪያ ወደ ቤት የገባ ሰው መልካም ዕድል ያመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ በዓሉን ያስጀምራል፡፡ በዓሉ ልዩ በሆነው የኤዲንብራ የጎዳና ላይ ፓርቲ፣ የሙዚቃ ዝግጅቶች እና ርችቶች ይደምቃል
  7. ኦሾጋትሱ የጃፓን አዲስ ዓመት፡- እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከጥር 1 እስከ 3 ቀን ይከበራል። አከባበሩ ቅዱስ ስፍራዎችን ወይም ቤተመቅደሶችን መጎብኘትን፣ እንደ "ኦሴቺ" (ባህላዊ ባለ ብዙ ንጣፍ የምግብ ሳጥን) ያሉ ልዩ ምግቦችን መብላትን ያካትታል። እንዲሁም "ኔንጋጆ" (አዲስ ዓመት ፖስት ካርድ) መላክም የበዓሉ አንዱ ገጽታ ነው። በተጨማሪም ሰዎች በዓመቱ የመጀመሪያ የፀሐይ መውጫ በሚሉት "ሃትሱሂኖድ" እና በዓመቱ የመጀመሪያው በሆነው "ሃትሱሞ" ዝግጅት ላይ ይካፈላሉ።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top