- ቀለብ እንዴት ይወሰናል እንዴትስ ይከፈላል?
- የአንድ ወላጅ ገቢ የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?
- አዲሱ የቀለብ አወሳሰን መመሪያ ምን ይዞ መጣ?
በቀለብ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሕፃናት ቀለብ አወሳሰን መመሪያ ቁ 1/2016ን አውጥቷል። ይህ መመሪያ ያስፈለገው ወላጆች ልጆችን የማሳደግ ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን፣ የቀለብ ጉዳይ የሕፃናቱን መብት እና ጥቅም ባስቀደመ፣ ወጥነት እና ተገማችነት ባለው መልኩ ፍርድ ቤቶች የቀለብ ክርክሮችን እንዲወስኑ ለማስቻል ነው። ይህ መመሪያ ለየትኞቹ አከራካሪ የቀለብ ጉዳዮች መፍትሄ እንደሰጠ ዛሬ እናያለን። ከዚያ በፊት ግን በቀለብ ጉዳይ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሰው አስገዳጅ ውሳኔ የተሰጠባቸውን የቀለብ ሙግቶች እናንሳ። እስከ ሰበር የደረሱ ሁለት የቀለብ ክርክሮችን ባጭሩ እንቃኛለን። በክርክሮቹ ላይ የተሰጡትን የመጨረሻ አስገዳጅ የሰበር ውሳኔዎች ከማንበባችሁ በፊት በቀለብ ጉዳይ ላይ ያላችሁን ግንዛቤ ለመፈተሽ የሰበር ውሳኔ ምን እንደሚሆን ገምቱና በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ውስጥ አጋሩን።
- አሳዳጊ ወላጅ በአደጋ ሲሞት ለሕፃኑ ቀለብ ማን ይስጥ?
የሕፃን የአብስራ አባት በአንድ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ተሳፍረው ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ሲጓዙ አባይ በረሃ ላይ በአሽከርካሪው የጥንቃቄ ጉድለት አውቶቢሱ መንገድ ስቶ በመውጣቱ በደረሰ አደጋ በ2004 ዓ.ም ይሞታሉ።
ሕፃኑ ገና አንድ ዓመቱ በመሆኑ እናቱ ሟች በወር 3 ሺህ 136 (ሦስት ሺህ አንድ መቶ ሠላሳ ስድስት) ብር እያገኙ እናቱን እና ሕፃኑን ሲያስተዳድሩ ስለነበር ሕፃኑ ለአካለ መጠን እስኪደርስ አባቱ በመሞቱ ምክንያት የተቋረጠ ገቢ በድምሩ ብር 395 ሺህ 816 (ሦስት መቶ ዘጠና አምስት ሺህ ስምንት መቶ አስራ ስድስት) እንዲከፍል የተሽከርካሪው ባለቤት የሆነው የሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት ድርጅት ላይ በፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ክስ ያቀርባሉ።
ተከሳሽም ተሽከርካሪው የመድን ዋስትና ያለው በመሆኑና የመጓጓዣ ዋስትና ከብር 40 ሺህ (አርባ ሺህ) ስለማይበልጥ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ እና ዋስትና ሰጪው የመድን ሰጪ ድርጅት ወደ ክርክሩ እንዲገባ ይደረግልኝ የሚል መልስ ሰጠ። መድን ሰጪውም የራሱን መከራከሪያ አቅርቦ ተከራከረ።
የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምን ይመስላችኋል? የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትስ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ያፀናዋል? ምን ትገምታላችሁ? ምላሻችሁን ከነ ምክንያቱ አስተያየት መስጫው ውስጥ አጋሩን።
- ስለ ሟች ልጅ ቀለብ ምን ተወሰነ?
የስር ፍርድ ቤት ክርክሩን መርምሮ ሟች በወር ያገኘው ከነበረው ብር 3 ሺህ 136 ላይ ብር 500 (አምስት መቶ) በየወሩ ወጪ ሊያደርግ ይችል እንደነበር ግምት ወሰደ። ሕፃኑ አንድ ዓመቱ በመሆኑ ለምግብ፣ ለልብስ፣ ለትምህርት፣ ለጤና እና ለሌሎችም ለመልካም አስተዳደግ አስፈላጊ ነገሮች የወር ወጪው ለቀጣይ 17 ዓመታት ሲሰላ በድምሩ ብር 102 ሺህ (አንድ መቶ ሁለት ሺህ) ሊያስፈልገው ቢችልም የጉዳት ካሳ መጠን በንግድ ሕጉ አንቀፅ 597 መሰረት ከ40 ሺህ (አርባ ሺህ ) ስለማይበልጥ ይህንኑ ብር የአውቶቢሱ ባለቤት ድርጅት እና መድን ሽፋን ሰጪ ድርጅቱ በአንድነት እና በነጠላ እንዲከፍሉ ወሰነ።
የሕፃኑ እናት ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ ብታቀርብም ተቀባይነት በማጣቷ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ስትል የሰበር አቤቱታ አቀረበች።
ሰበር ሰሚ ችሎት ሁለት ጭብጦችን ይዞ በመመርመር የንግድ ሕጉን የአጓጓዥ ኃላፊነት መጠን ገደብ ለቀለብ ጉዳይ አግባብነት የሌለው በመሆኑ የስር ፍርድ ቤት ከዚሁ ገደብ ጋር በማያያዝ ብር 40 ሺህ ብር ብቻ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን አብራርቷል። የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔም ወደ ፊት የሟች ገቢ ሊያድግ የሚችልበትን እና የልጁም መሰረታዊ ፍላጎቶች ወጪ በየጊዜው ከፍ እያለ መሄዱን ያላገናዘበ መሆኑን ተችቷል። የቀለቡን መጠን ከወዲሁ መወሰኑ አስቸጋሪ መሆኑን በማንሳትም የስር ፍርድ ቤት ለግምቱ መነሻ ያረገውን 500 (አምስት መቶ) ብር ወርሀዊ ወጪ ወደ 1 ሺህ (አንድ ሺህ) ብር በማሳደግ ለ17 ዓመታት ሲሰላ የሚመጣውን ብር 204 ሺህ (ሁለት መቶ አራት ሺ) በአንድ ጊዜ የሕፃኑ ሞግዚት ለሆነችው ለእናቱ ገቢ በማድረግ እንዲከፈል ወስኗል። አከፋፈሉንም በተመለከተ ብር 40 ሺህ ድርጅቱ እና መድህን ሽፋን ሰጪው አንድነት እና በነጠላ ቀሪውን ብር 164 ሺህ ደግሞ አጓጓዥ ድርጅቱ ብቻውን ይክፈል ሲል ወስኗል። ውሳኔውን ሕዳር 19 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰ.መ.ቁ.109061 የሰጠው ሲሆን፣ በሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 20 ላይ ታትሞ ወጥቷል።
- የቀለብ ሰጪ ገቢ
አቶ በላይ እና ወ/ሮ ትግስት በ2004 ዓ.ም ሴት ልጅ ያፈራሉ። ሕፃኗ ከጋብቻ ውጭ በመወለዷ የአቶ በላይ አባትነት በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተረጋገጠ በኋላ ወ/ሮ ትዕግስት በ2007 ዓ.ም ለሕፃኗ ቀለብ አቶ በላይ 5 ሺህ 750 (አምስት ሺህ ሰባት መቶ ሀምሳ) ብር በየወሩ እንዲከፍሉ እና ነዋሪነታቸው ሲውዘርላንድ በመሆኑ ሕፃኗ 18 ዓመት እስኪሞላት ሳያቋርጡ ቀለብ መክፈላቸውን ዋስ ወይም መያዣ እንዲያቀርቡ ወይም ቀለቡ ተሰልቶ ባንድ ጊዜ በባንክ ሂሳባቸው ገቢ እንዲያደርጉ ለፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ክስ ያቀርባሉ።
አቶ በላይ ክሱ ሲደርሳቸው ገቢያቸው በወር 4 ሺህ (አራት ሺህ) ብር የማይሞላ መሆኑን፣ ለሌላ ልጅ ቀለብ እንደሚቆርጡ፣ ዕዳ እንደሚከፍሉ እና ሌላ ትዳርም እንዳላቸው በመጥቀስ መክፈል የሚችሉት በወር 1 ሺህ (አንድ ሺ) ብር ብቻ በመሆኑ በዚሁ ይወሰንልኝ ሲሉ መልስ ሰጡ።
የስር ፍርድ ቤት እና የሰበር ውሳኔ ምን የሚሆን ይመስላችኋል?
ፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት አቶ በላይ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማስረጃ ያልተደገፈ ነው ሲል አልተቀበለውም። በተጨማሪም በክርክሩ ላይ ከቤት ሽያጭ አቶ በላይ ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘታቸውን እና ከኢትዮጽያ ውጭም ገቢ እንዳላቸው በመረጋገጡ በወር 4 ሺህ (አራት ሺህ) ብር እንዲከፍሉ፣ ወ/ሮ ትዕግስት በጠየቁት መሰረት የስድስት ወር ቀለብ በአንድ ጊዜ ገቢ እንዲያደርጉ፣ ሕፃኗ 18 ዓመት እስኪሞላት ለሚፈለግባቸው የ14 ዓመት ከ6 ወር ቀለብ ሲሰላ የሚመጣውን ብር 696 ሺህ (ስድስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ) ብር ክፍያ ዋስትና የሚሆን ዋስ እንዲጠሩ ወይም መያዣ እንዲያስይዙ ካልሆነም በአንድ ጊዜ ገንዘቡን በወ/ሮ ትዕግስት የባንክ ሂሳብ ገቢ እንዲያደርጉ ወሰነ።
አቶ በላይ ይህን ውሳኔ በመቃወም በየደረጃው አልፈው ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ ቀለብ በወር 1 ሺህ (አንድ ሺህ) ብር ብቻ ልክፈል ሲሉ ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ ሰጥቶበታል።
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ.130931 ሰኔ 19 2009 ዓ.ም በሰጠውና የሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 21 ታትሞ በወጣው ውሳኔው የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶታል።
- አዲሱ መመሪያ ምን ይዞ መጣ?
የሕፃናት ቀለብ አወሳሰን መመሪያ ቁ. 1/2016 የወጣው ከላይ ያየናቸው መሰል ክርክሮች ላይ ፍርድ ቤቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና ሀገራችን የፈረመቻቸው የሕፃናት መብት ኮንቬንሽኖች የሕገ መንግሥቱ አካል ተደርገው ስለሚቆጠሩ ፍርድ ቤቶችም እንደሌሎች የመንግሥት ተቋማት የሕፃናትን ጥቅም እና ደህንነት የሚያስጠብቅ አሠራር በመዘርጋት ግልፅ፣ ወጥ እና ተገማች የቀለብ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ለማገዝ መሆኑን መመሪያው በመግቢያው ላይ ይገልጻል።
በተጨማሪም ለሕፃናት መብት እና ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የቀለብ ክርክር ጊዜ ሳይፈጅ፣ የሕፃናትን የመኖር እና ምቹ ሁኔታ ውስጥ የማደግ መብትን፣ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው አቅሙ የፈቀደውን ቀለብ እንዲሰጥ ማስቻልን፣ ቀለብ ሚወሰንበትን አግባብ ወላጆች በቀላሉ እንዲረዱት ለማስቻል ሲባል ነው መመሪያው የወጣው።
- የመመሪያው ተፈፃሚነት
መመሪያው በፌደራል እና በየትኛውም የቀለብን ጉዳይ በሚወስን ፍርድ ቤት ተፈፃሚነት አለው። ከሕፃናት ጉዳይ ባሻገርም አካለ መጠን ከደረሱ በኋላ በተለያየ የጤና ነክ እና ተያያዥ ምክንያቶች መሰረታዊ ነገርን ማሟላት ባለመቻል የሚነሳ የቀለብ ጥያቄን ለመወሰንም ሊውል እንደሚችል ተጠቅሷል።
- የቀለብ አወሳሰን መርህ
በመርህ ደረጃ የወላጆችን ቀለብ የመስጠት ችሎታ፣ የሕፃኑን ወላጆቹን የማወቅ እና እንክብካቤ የማግኘት መብት፣ እንደ ኢኮኖሚያዊ ገቢያቸው መጠን ወላጆች የቀለብ ድርሻን ሊጋሩ በሚችሉበት አግባብ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሥራ አለመሥራቱ ካልተረጋገጠ በስተቀር ሥራ አለመሥራት ብቻውን ከቀለብ ተጠያቂነት እንደማያድን፣ የሕፃኑን መሰረታዊ ፍላጎት እና ልዩ ወጪዎችን ባገናዘበ እና የወላጆችን ገቢ፣ ወጪ እና ሕጋዊ ተቀናሾችን፣ የቀለብ ተቀባዮችን ቁጥር፣ የዕድሜ እና የጤና ሁኔታዎች ከግምት አስገብቶ እንዲሁም ከኑሮ ግሽበት እና ከገቢ መጨመር ለውጦች ጋር ሊሻሻል በሚችል መልኩ የቀለብ ጥያቄ መወሰን እንዳለበት መመሪያው ያስቀምጣል።
- ቀለብ እና ገቢ
ቀለብ የሚወሰንበት የገቢ ምንጭን በተመለከተ በመመሪያው አንቀፅ 18 ስር የቀለብ ሰጪው የገቢ ምንጮች ተብለው የሚወሰዱ የገቢ ዓይነቶች ተቀምጠዋል።
ቀለብ ሰጪው ተቀጣሪ ሠራተኛ ከሆነ ደመወዝ፣ ለተጨማሪ ሥራ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች፣ ጉርሻዎች፣ የተለያዩ አበሎች የፕሮቪደንት ክፍያዎች እና ከቅጥር ጋር የተያያዙ ማንኛቸውንም ገቢዎች ሊያካትት ይችላል።
ቀለብ ሰጪው በግሉ የሚሠራ ከሆነ ዓመታዊ ወይም ወርሀዊ ገቢው፣ በተለያዩ ቦታዎች ለሚሠራው ሥራ ሚከፈለው ክፍያ እና ከግል ሥራው ጋር የተያያዙ ገቢዎች ሊያካትቱ ይችላሉ።
ቀለብ ሰጪው ጡረተኛ ከሆነ ደግሞ ገቢው የጡረታ አበል እና ማንኛውንም ሌላ ገቢ የሚያካትት ነው።
ቀለብ ሰጪው በማንኛውም የሥራ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም የቤት ወይም የተሽከርካሪ ኪራይ ወይም ሽያጭ ገቢ፣ የባንክ ተቀማጭ፣ ወለድ፣ ብድር ገቢ፣ የሎተሪ ወይም የማንኛውም ውድድር ሽልማት፣ የካሳ ክፍያ ወይም ማንኛውም ሌላ ገቢ እንደሚያካትት መመሪያው ይደነግጋል።
- ገቢ እንዴት ይታወቃል?
ፍርድ ቤቱ የቀለብ ሰጪን ገቢ ለማወቅ ለአሠሪ፣ ለገቢዎች፣ ለባንክ ወይም ተገቢ ነው ለሚለው ለማንኛውም አካል ትዕዛዝ መስጠት ይችላል። ከላይ ባሉት ሁኔታዎች መሰረት የቀለብ ሰጪን ገቢ ማወቅ ካልተቻለ ደግሞ በወላጆች መለያየት ለቀረበ የቀለብ ጥያቄ ከወላጆች መለያየት በፊት ይወጣ በነበረ የቀለብ ወጪ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ መስጠት ይቻላል።
- ምን ያህሉ ገቢ ለቀለብ?
ከነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ የሆነው ይህ መመሪያ ቀለብ የሚሰላበትን የገቢ ሰንጠረዥ አስቀምጧል።
በዚህ ሰንጠረዥ መሰረት እስከ ብር 2 ሺህ (ሁለት ሺህ) ወርሀዊ ገቢ የሚያገኝ ቀለብ ሰጪ የገቢውን 24 በመቶ ለአንድ ሕፃን፣ ለ2 ሕፃናት 36 በመቶ፣ ለ3 ሕፃናት 42 በመቶ፣ ለ 4 ሕፃናት 45 በመቶ፣ ከ4 በላይ ከሆኑ 48 በመቶ ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ያስቀምጣል።
የቀለብ ሰጪው ወርሀዊ ገቢ በጨመረ ቁጥርም የቀለብ መጠኑ የምጣኔ ስሌት እየቀነሰ ይመጣና በወር ከ100 ሺህ-200 ሺህ (ከመቶ ሺህ አንድ እስከ ሁለት መቶ ሺህ) ብር የሚያገኝ ቀለብ ሰጪ ለአምፍ ሕፃን ሚከፍለው የወር ገቢውን 21 በመቶ ሲሆን፣ እየጨመረ ሄዶ ከአራት ሕፃናት በላይ ከሆነ 35 በመቶ ይሆናል።
ቀለብ ሰጪ ወርሀዊ ገቢው ከብር 200 ሺኅ (ሁለት መቶ ሺህ) በላይ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የሕፃኑን ፍላጎት ባማከለ መልኩ ከሰንጠረዡ የስሌት ምጣኔ ያላነሰ ቀለብ መወሰን ይችላል።
ነገሩን ስንቋጨው በጋብቻ ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ባሉ ሁኔታዎች ሕፃናትን በተመለከተ የሚወሰኑ የቀለብ እና ሌሎች ውሳኔዎች ከላይ ባነሳነው መልኩ ሕፃናቱን ያስቀደሙ መሆን አለባቸው።
ኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)