8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ

27 Days Ago 15041
8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ

በአውሮፓውያኑ 2007 በአፍሪካ ሕብረት የተበሰረው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ የአህጉሪቱን የተራቆተ መልክዓ ምድር አረንጓዴ በማልበስ በሳህል ቀጠና የሚኖሩ ሚሊዮኖችን ህይወት የመለወጥ ዓላማ ያለው ፕሮጀክት ነው።


በፕላኔታችን ላይ ካሉት የሥነ-ህይወት ፕሮጀክቶች ሁሉ ትልቁ እንደሆነ የተነገረለት እና በአፍሪካ ውስጥ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ ዘላቂነት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስፈን ታልሞ የተጀመረ ነው።


ይህ ፕሮጀክት በ22 የአፍሪካ ሀገራት እየተተገበረ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያንቀሳቅሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።


ይህን ፕሮጀክት ለመደገፍ ከ14 ቢሊየን ዶላር በላይ መሰባሰቡም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረሃማነትን የመዋጋት ኮንቬንሽን (United Nations Convention to Combat Desertification) ገጽ ላይ ተመላክቷል።


ዓለማውም በአውሮፓውያኑ 2030 በአሁኑ ወቅት ወደ በረሃማነት የተለወጠውን 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ አረንጓዴነት በመመለስ 250 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ማመንጨት እና 10 ሚሊዮን አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡


ስለተፈጥሮ እና ስለምድራችን ፈተናዎች የሚዘግበው ሞንጋቤይ (Mongabay) የተባለ ድረገጽ ባወጣው መረጃ በረሃማነትን ለማስቆም የሚደረገውን ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ ቢሆንም ተስፋ የሚጣልበት ውጤት እያሳየ ነው፡፡


ድረ-ገጹ ያናገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን ዛፍ የመትከል ብቻ ሳይሆን አካባቢውን የሚለውጥ እንዲሁም የገቢ ምንጭ እንደሆነ አድርጎ እንዲመለከተው ግንዛቤ በመፍጠር ሁለንተናዊ ተሳትፎን እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡


በዚህ መንገድ ተሞክሮም በማሊ፣ ቡርክናፋሶ፣ ኒጀር፣ ጋና እና በሌሎች ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ውጤታማ እንደሆነ ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ስኬቶች እና ቀጣይ ጉዞ


ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ አደገኛነት የተረዳችው ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጀምራለች፡፡


ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከተተከሉት 32 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 90 በመቶው መጽደቃቸው ተገልጿል፡፡


በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ኮንቬንሽን መስፈርት መሰረትም በ2011 ዓ.ም 17.2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በአሁኑ ጊዜ 23.6 በመቶ ደርሷል፡፡


ኢትዮጵያ ደኗን ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ወደ ነበረው 40 በመቶ ለመመለስ ስትራቴጂ ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በ2030 አሁን ያለውን 23.6 በመቶ የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስም እየተሠራ ነው፡፡


ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጎን ለጎን የደን ምንጣሮን የመቀነስ ሥራም ስለተሠራ ዓመታዊ የደን ውድመት ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺህ ሄክታር ቀንሷል፡፡ አዳዲስ ችግኞችን መትከል እና የደን ጭፍጨፋን መቀነስ መቻሉ የደን ሽፋን እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡


በባለፈው ዓመት መርሐ-ግብር 60 በመቶ የጥምር ደን እርሻ ችግኞች፣ 35 በመቶ ደግሞ የደን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ችግኞች ነው መትከል የተቻለው፡፡


በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ እና አፕል ያሉ ተክሎች የምሥራች ፌሬያቸውን ሰጥተው ለምግብነት ደርሰዋል፡፡


ይህ መርሐ ግብር ኢትዮጵያውያን በየጓሮአቸው ችግኞችን ተክለው የሚንከባከቡበትን ባህል ፈጥሯል፡፡
በዚህ ዓመት ደግሞ 43.9 በመቶ ለደን እና ውበት፣ 56.1 በመቶ የጥምር ደን እርሻ (ለፍራፍሬ እና ለመኖ) ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተው "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል ተከላው እየተካሄደ ነው፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ እንዲሸለሙ ካደረጉአቸው ስኬቶች አንዱ የአረንጓዴ አሻራ ውጤታማነት ነው፡፡


በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top