በሀቅ ኖረው፤ ታምነው ያለፉት የሕዝብ ባለአደራ፡- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

10 Hrs Ago 291
በሀቅ ኖረው፤ ታምነው ያለፉት የሕዝብ ባለአደራ፡- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

ከያኒው "…ሞት እንኳን ጨክኖ ወስዶ ከሚያስቀረው፣

            ምን አለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው።" እንዳለው ሞት የሀገር ዋርካውን፣ የሕዝብ ተሟጋቹን፣ የሚሊዮኖች የቀለም አባትን ጨክኖ ወሰዳቸው፡፡ በእርግጥ በሠሯቸው መልካም ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ለዘላለም የሚኖሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህያው ናቸው፡፡

ትህትና፣ የሕዝብ ፍቅር፣ ታታሪነት እና የተግባር ሰውነት መገለጫቸው ነው፡፡ የብዙኃን ድምፅ ሆነው በሕዝብ ላይ የከፋ ግፍ እና በደል እንዳይፈፀም ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ ኖረዋል። ፖለቲካ ንግድ በሆነበት ሀገር ከሕዝብ ምንም ሳይወስዱ ራሳቸውን ለሕዝብ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ. ኬኔዲ አባባል ነው ተብሎ የሚነገረውን "ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረግሁላት" ማለት አለብን ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲጠቅሱም እኛ ለሀገራችን ሠርተን ሀገራችንን ካልለወጥን ሀገር ከየትም አምጥታ ልትሰጠን አትችልም በማለት ፡፡  

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሕይወት እያሉ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዓውደ ሰብ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ አሜሪካ ተምረው ወደ ሀገራቸው ሲመጡ ያጋጠማቸውን አጋርተውን ነበር፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፓስፖርታቸውን ለማሳደስ ይሄዳሉ፤ አምባሳደሩን ጨምሮ የኤምባሲ ሠራተኞችም በዚህ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የምትሄደው አብደሃል እንዴ አሏቸው፡፡ እሳቸውም ግድ ወደ ሀገሬ መሄድ አለብኝ በማለት ፓስፖርታቸውን አሳድሰው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን የጠበቃቸው የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል አልነበረም፤ ፓስፖርታቸው ተቀምቶ ከአንድ ወር በኋላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠይቀህ ውሰድ ተባሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሚያውቁት ዘመድ እንደሌላቸው የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር ሆቴል ለማረፍም መታወቂያ ስላልነበራቸው ተንገላትተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው ወደ መጡበት ለመመለስ ወይም ለማማረር አልፈለጉም፡፡ ምክንያቱም ለሀገር እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነበሩና፡፡

ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ተምረው ሲመጡም የገጠማቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ እንሚመለስላቸው ቃል የተገባላቸው መኖሪያ ቤት ለሌላ ሰው ተሰጥቶ ጠበቃቸው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሄደው ቢጠይቁም የሚያስተናግዳቸው ጠፋ፤ ልጆቻቸውን ይዘው ብዙ ተንከራተቱ፡፡ በዚህም ምን አለ ወደ ኢትዮጵያ ባልተመለስኩ አላሉም፤ ለችግራቸው መፍትሔ አበጅተው ሀገራቸውን ማገልገል ቀጠሉ፡፡

ኢትዮጵያን ሊለውጥ ይችላል ብለው የሚያምኑበትን ሃሳብ ለመቀበል ቅድመ ሁኔታ አያስቀምጡም፡፡ መምህርነት እና ፖለቲከኛነት አልተጋጨባቸውም፡፡ ትምህርት ቤት ሲሆኑ ምርጥ አስተማሪ እና ተመራማሪ፣ በፖለቲካው መድረክም የሃሳብ ተሟጋች ናቸው፡፡ ፖለቲካንም ሆነ አስተማሪነት ሳይቀላቅሉ በየራሳቸው መድረክ አሳምረው ይወጡአቸዋል፡፡

ከሦስት አሥርት ዓመታት በተሻገረው የአደባባይ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ብዙ ችግሮችን በግጭት እና በጠመንጃ አፈሙዝ መፍታት መሞከር ልማድ በሆነባት ኢትዮጵያ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገው በጠመንጃ መሸናነፍ ሳይሆን የሃሳብ ሜዳ መሆኑን በተግባር አስመስክረዋል፡፡

በመምህርነት እና ተመራማሪነት የብዙዎችን የህይወት መንገድ አቃንተዋል፤ በፖለቲከኛነታቸውም ህዝባቸውን ወክለው ተከራክረዋል፤ ባገኙአቸው መድረኮች ሁሉ ሳይሰለቹ የህዝብን ትክክለኛ ጥያቄ አሰምተዋል፡፡

ብዙ የቀድሞ ተማሪዎቻቸው የሚያውቁአቸው በታታሪ መምህርነታቸው እና Introductory to Basic Biology በሚለው መጽሐፋቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሰለማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በመምህርነት እንዲሁም በሽግግሩ ዘመን የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 07 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተወለዱት መጋቢት 1942 ዓ.ም በሃዲያ ምሰራቅ ባዶዋቾ ሾኔ ከተማ አቅራቢያ ባለችው ገጠራማ መንደር ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የምስራቅ ባደዋቾ ዋና ከተማ በሆነችው ሾኔ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዳማ በሚገኘው የቀድሞ አጼ ገላዎዴዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ህይወት (Biology) የትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል፡፡ አዳማ አፄ ገላውዴዎስ ሲማሩ በሳይንስ ክለብ አማካኝነት ያዩዋቸው ዶክተር አክሊሉ ለማ በሳይንስ ላይ የሠሩትን ሥራ አርአያ አድርገው ስለነበር ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የመረጡት የትምህርት ዘርፍ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውም የላቀ ውጤት በማምጣታቸው እዚያው ጀማሪ መምህር ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የውጭ መምህራንን በኢትዮጵያውያን ለመተካት ሲያደርገው በነበረው ጥረት ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲማሩም ተደረጉ። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ዊስከንሲን ዩኒቨርሲቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም እዚያው አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ቱለን ዩኒቨርሲቲ በህዝብ ጤና እና በተላላፊ በሽታዎች (Tropical Diseases) ሠርተዋል፡፡

ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1970 ቀጥታ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ከ1978 እስከ 1982 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ 

በተላላፊ በሽታዎች (Tropical Diseases) ላይ በርካታ ምርምሮችን ከሥራ አጋሮቻቸው እና ተማሪዎቻቸው ጋር አከናውነዋል። በተለይም በወባ መሽታ፣ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ፣ በሳምባ ነቀርሳ፣ እንዲሁም በርከት ባሉ ሌሎች ህዋስ ወለድ በሽታዎች ላይ ሰፊ ምርምር አድርገዋል። ባልተሟሉ የቤተ ሙከራዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ በተለይ ኤችአይቪ/ኤድስ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ስላለው ግንኙነት እና በምድር ወገብ ሀገራት አካባቢ ስላለ በሽታ ወለድ ህዋሳት ባህሪ በማጥናት ከአንድ መቶ በላይ በርካታ ምርምሮች በዓለም አቀፍ መድረኮች ይፋ አድርገዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በርካታ ወጣት ተመራማሪዎችን በመምራት እና በማስተባበር ለውጤት ያበቋቸው ምርምሮች በሥነ ህይወት ሳይንሱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ እና በሀገር ቤት ባበረከቱት ድርሻም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።

በሂደት ባደጉበት አካባቢ ህዝብ ላይ ይደርስ የነበረው ጭቆና እና የህዝቡ በመሬቱ ላይ ባለቤት አለመሆኑ የመሬት ጥያቄን ሲያነሳ ወደ ነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳቡ፡፡ የፊት መሪ ባይሆኑም በነበረው እንቅስቃሴ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በ1983 ኢህአዴግ ኢትዮጵያን መምራት ሲጀምር የፊት ለፊት ፖለቲካውን በግልጽ ተቀላቀሉ፡፡ በሽግግሩ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ተሹመው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰነ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡ በዚህ የኃላፊነት ወቅት የሚታወቁበት አንድ ጉዳይም አለ፡፡ የግል ቤት ስላለኝ ቤትም ሆነ የቤት አበል አልቀበልም ማለታቸው፡፡

ግንቦት 1992 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሃዲያ ዞን የምትገኘው ሾኔን በመወከል  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። የፓርላማ አባል በነበሩበት ወቅት ለአባላቱ የሚከፈላቸውን ደመወዝም ሆነ ቤት አልተቀበሉም፤ ለዚህም ምክንያታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደመወዝ ስለሚከፈላቸው እና የግል ቤት ስላላቸው መሆኑን ራሳቸው ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ጠላት ስለሌላት እጅግ ውድ ወጪ የሚጠይቅ አየር ኃይልም አያስፈልጋትም የሚለውን የአህአዴግ አቋም በመቃወም የአየር ኃይሉ ህልውና እንዲጠበቅ በምክንያት ተከራክረዋል። ኢትዮጵያ በየብስ፣ በባህርም በአየርም ሠራዊት ሊኖራት እንደሚገባም ቀድመው ሲከራከሩ የነበሩ አርቆ አሳቢ ናቸው።

የሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ የመናገር እና የመጻፍ ነጻነት፣ የመደራጀት እና ከትጥቅ ትግል ውጭ የትኛውንም የፖለቲካ አመለካከት የመያዝ፣ የማራመድ እና የመደገፍ መብት እንዲጠበቅ በብዙ ተሟግተዋል፡፡

የህዝብን ድምፅ ለማሰማት ያሉትን የጠበቡ እድሎች ታግሎ በማስፋት፣ ሰላማዊ መንገድን በመከተል ባለው አጋጣሚ በተገቢው ቦታ ለመገኘት መታገል እንደሚያስፈልግ የሚያምኑት ፕሮፌሰር በየነ ይህንኑ እምነታቸውን በተግባር ኖረው አስመስክረዋል።

ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿ እና ከውጭ ጫናዎች መላቀቅ የምትችለው የውስጥ አንድነቷን ስታጠናክር መሆኑን የሚያምኑት ፕሮፌሰር በየነ፣ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ተቆጥበው አያውቁም፡፡

ኢትዮጵያ የሚገጥሙአት ፈተናዎች አዲስ እንዳልሆኑ እና ፈተናዎቹን ለማለፍ ግን የሰከነ አካሄድ እና ቅድሚያ ለሚሰጡ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ለችግሮች መፍተሔ እየሰጡ ስለመሄድ ሲናገሩ፣ “እኔ ኢትዮጵያ ዜጎቿን የማትጠቅም ሀገር ሆና ትቀጥላለች ብዬ አላምንም፤ ከእምነት አንፃር ተነስተው የሚናገሩ አሉ፣ ከእውነት አንፃር ተነስተው የሚናገሩም አሉ። እኛ ብቻ አይደለንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለነውም እያለፍን ያለነውም፡፡ ስለዚህ ስለጎደለብን ነገር ብቻ እያብሰለሰልን መኖር አይገባንም። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም ወደ ፊት ለመሄድ መነሳት አለብን። ለጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት አለብን፤ በቅድሚያ መፍትሄ መስጠት የምንችለውን አሁን ፤ በይደር እና በሂደት መፍትሄ የምንሰጠውን ጉዳይ በሂደት ለመፍታት የሚሰራ እና ትዕግስት ያለው ፖለቲከኛ ያስፈልገናል" በማለት ይገልፁ ነበር።

ለኢትዮጵያ ስላላቸው ፍቅር ሲገልጹም፣ “በኢትዮጵያዊነቴ ያልኮራሁበት አጋጣሚ የለም፣ እኔ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተስፋ አልቆርጥም። እዚህ እንድደርስ በርካታ ዘመዶቼ፣ ወዳጆቼ እና ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ አስተዋፅኦ አድርገዋል።  እናም በህይወቴ በኢትዮጵያዊነት ክብር የሚሰማኝ ሰው ነኝ” ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰር በየነ እጅግ የተለየ የሥራ ባህል ያላቸው ናቸው። "24 ሰዓት ለሁሉም ነገር በጣም በቂ ነው" የሚል እምነት ስላላቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጊዜ አጠረኝ የሚል ምክነያት እርሳቸው ጋር አይሠራም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ጊዜ መምህር እና አማካሪነታቸው ለተማሪዎቻቸው፣ ለጥናት ወረቀቶች እርማት እና ግምገማ፣ ለሳይንሳዊ ምርምር ስራዎች በቂ ጊዜ መድበው ይሰራሉ። ምርምሮችን በጥልቀት ይፈትሻሉ ማሻሻያዎችን ለተማሪዎቻቸው ይሰጣሉ። ሙሉ የስራ ሰዓታቸውን ለመደበኛ ስራቸው ከማዋል በተጨማሪ ቤታቸውም ጊዜ ወስደው ያርማሉ ያስተካክላሉ። ይህን የማስተማር ኃላፊነታቸውን በሙሉ ጊዜ ከማከናወን ጎን ለጎን ነው እንግዲህ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን የሚያደርጉት፡፡

ኢትዮጵያ ጥሪቷን አሟጣ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ዝምታ እና የዳር ተመልካችነት የሚያንገበግባቸው ፕሮፌሰር በየነ፣ ምሁራን ሀገራቸውን የሚለውጥ ሥራ ላይ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራሉ፤ ሀገራቸው ያስተማረቻቸውን እውቀት እና የሰጠቻቸውን እድል በመጠቀም ማኅበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጎትጉተዋል።

ኑሮን ቀለል አድርጎ መኖር፣ የመንፈስ ስብራት፣ ላመኑበት ጉዳይ ዋጋ መክፈል፣ ትህትና፣ የመርህ ሰውነት፣ እውነተኛነት፣ ማኅበራዊ ተሳትፎ እና ወጥነት የፕሮፌሰር በየነ መገለጫወቻቸው እንደሆኑ ተማሪዎቻቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና አብሮ አደጎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ 

ነሐሴ 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ላለመው የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተቋቋሙት የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤቶች መካከል የፕራይቬታይዜሽን አማካሪ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል። 

ሀገርን የሚያስቀድም እና የሚጠቅም ከሆነ ከማንም ጋር ለመሥራት ችግር የሌለበቸው ፕሮፌሰር በየነ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትን እስከ እልፈተ ሕይወታቸው  በሃላፊነት መሥራታቸው ለዚህ አቋማቸው ዋቢ ነው፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በህዝብ ተሳትፎ፣ በትምህርት እና በምርምር አመራር በርካታ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ሽልማቶችን እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።

120 ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶቸን ለብቻቸው እና በጋራ በመሆን በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ያሳተሙ ሲሆን፣ "Basic Principles of Biology" የተባለ ተወዳጅ መጽሐፍም አዘጋጅተዋል።

ሰው ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ ካሳካ አረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፡፡ ፕሮፌሰር በየነም ምንም ሳይሰስቱ ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በርካታ ምሁራንን አብቅተው ለሀገር አበርክተዋል፡፡ ለሀገር እና ለትውልድ የሚተርፍ በርከታ ተግበራትን የከወኑት ታላቁ ምሁር፣  የህዝባቸውን ችግር በማሰማት ፊት ለፊት የታገሉት የሰላማዊው ትግል ተምሳሌት ፖለቲካኛው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በዛሬው ዕለት ስርአተ ቀብራቸው ተፈፅሟል፡፡  እኝህ ታላቅ ሰው በሥራዎቻቸው ህያው ሆነው ሀልጊዜም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top