ኢትዮጵያ በቡድን 24 የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የብሄራዊ ባንክ ገዥዎች ስብሰባ ላይ ተሳተፈች

3 Hrs Ago 27
ኢትዮጵያ በቡድን 24 የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የብሄራዊ ባንክ ገዥዎች ስብሰባ ላይ ተሳተፈች

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑክ በቡድን 24 የገንዘብ ሚንስትሮች እና የብሄራዊ ባንክ ገዥዎች ስብሰባ ላይ ተሳትፏል።

ኢትዮጵያ እየተሳተፈችበት ያለው የዓለም ባንክ እና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የ2024 አመታዊ ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው፡፡

የጉባኤው አካል የሆነው የቡድን 24 የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የብሄራዊ ባንክ ገዥዎች ስብሰባ በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በስብሰባው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ ተሳትፈዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአለም ባንክ እና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው የረዥም ጊዜ አጋርነት አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡

የተቋማቱ ድጋፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ሀገራት ቀውስ ባጋጠማቸው ጊዜ እሴታቸውን በቀላሉ ወደ ገንዘብ ለመቀየር ፈጣን አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

እያደጉ ያሉ ሀገራት በተመጣጣኝ ወለድ የዕዳ ጫና ሳይፈጠርባቸው ሀብት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ሀገራት ከኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን አንጻር በቂ ገንዘብ ማግኘት እንዲችሉና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በስብሰባው ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑኩ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የብሪተን ጉድስ ሲስተም (Breton Woods system) ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ማስረዳቱን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top