16ኛውን የብሪክስ ጉባኤ እያስተናገደች ያለችው ካዛን ከተማ

3 Hrs Ago 29
16ኛውን የብሪክስ ጉባኤ እያስተናገደች ያለችው ካዛን ከተማ

የባለብዙ ባህል ባለቤት የሆነችው ካዛን ከተማ 16ኛውን የብሪክስ ጉባኤ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

ከ150 በላይ የብሄር ማንነቶች በሰላምና በአብሮነት፣ ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ካዛን የብዘኃ ሃይማኖቶች፣ ባህልና ማንነቶች መገኛ የሆነች ታሪካዊ ከተማ ነች፡፡

ሩሲያ የ2024 የብሪክስ ጉባኤን በካዛን ለማስተናገድ የመረጠችው አንደኛው ምክንያት ከተማዋ ብዘኃነት የሚስተናገድባት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋና ማንነት ያላቸው ህዝቦች በሰላም ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ ነው፡፡

በኃይማኖቶችና በብዙ ማንነቶች መካከል ያለው ሰላማዊ ግኑኝነትና አብሮ የመኖር ባህልና እሴት ከተማውን ተመራጭ አድርጎታልም ነው የተባለው፡፡

1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚኖሩባት ካዛን የሩሲያ የብዘኃነት መገኘ ከተማ ብቻ አይደለችም ይልቁንም በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የድፍድፍ ዘይት ማጣሪያ፣ የኤሌክትሪክና ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች መገኛ እንዲሁም የንግድ ማዕከልም ነች፡፡

የምዕራቡንና የምስራቁን ባህል አጣምራ እንደያዘች የሚነገርላት ካዛን ከተማ በርካታ ጥንታዊ የኪነ ህንጻ ጥበቦች የሚታዩባት ከተማም ነች፡፡

ከተማዋ በታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኩል ሸሪፍ መስኪድ ባለቤት ስትሆን በብዙ ቱርስቶች የሚጎበኝ መስኪድ ነው፡፡

ካዛን 5ኛዋ የሩሲያ ትልቋ ከተማ ስትሆን ከሞስኮ በስተምስራቅ 719 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ታሪካዊ ከተማ ነች፡፡

የደቡብ ዋልታ አስተሳሰቦችን ያጣመረው የብሪክስ ጥምረት በ16ኛ ጉባኤው በአባል ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየመከረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈችበት ባለው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸው ኢትዮጵያን ወክለው በሩሲያ ካዛን እየተሳተፉ ይገኛል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top