41 በመቶ የዓለምን ህዝብ የያዘው ጥምረት ምን አለው?

7 Hrs Ago 25
41 በመቶ የዓለምን ህዝብ የያዘው ጥምረት ምን አለው?
የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካን የመጀመሪያ ፊደል በመውሰድ የተሰጠ ስያሜ ነው ብሪክስ (BRICS)።
 
የተጠቀሱት መስራች ሀገራትን ጨምሮ በቅርቡ የተቀላቀሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳውዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ አባል ሀገራቱ ናቸው።
 
ብሪክስ በአባላቱ መካከል የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የልማት፣ የፋይናንስ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ትብብርን ማጠናከርን መዳረሻው አድርጓል።
 
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ሀገራትን የሚያካትተው ስብስቡ በአኀዝ ሲገለፅ ይህን ይመስላል፡-
 
• ቱርክ እና ኢንዶኖዢያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ከ40 በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራትም ጥምረቱን የመቀላቀል ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
 
• የብሪክስ አባል ሀገራት 41 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ የያዙ ናቸው።
 
• 35 በመቶ የሚሆነውን የዓለማችንን የሀገር ውስጥ ምርትን ሲሸፍኑ፤ ቻይና ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች።
 
• ሀገራቱ 26 በመቶ የሚሆነውን የምድራችንን ቦታ ሲይዙ፤ ሩሲያ 17.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ቦታ ትሸፍናለች።
 
• የመስራቾቹ ሀገራት የውጭ ምንዛሬ ክምችት 4.8 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን ቻይና 3.2 ትሪሊዮን ዶላር በመያዝ ቀዳሚዋ ናት።
 
• በዓለም አቀፍ ገበያ 20 በመቶ የሚሆን አስተዋፆ ያላቸው ሀገራቱ በገቢ እና ወጪ ንግድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ናቸው፤ በዚህ ረገድ የዓለማችን ከፍተኛዋ የምርት ላኪ ሀገር የሆነችው ቻይና ስብስቡን ትመራለች።
 
• ሀገራቱ 40 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የኃይል ሐብቶችን በመቆጣጠር፣ በኃይል ገበያ ዘርፍ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
 
• አዲስ ልማት ባንክ በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ በ2014 በ100 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ተቋቁሟል።
 
ባንኩ ከ90 በላይ የመሠረተ ልማት፣ የኢነርጂ፣ የትራንስፖርት እና ማህበራዊ ፕሮጀክቶች ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፋይናንስ አጽድቋል።
 
የብሪክስ አባል ሀገራት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ የኢነርጂ ሐብቶች፣ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶች እንዲሁም ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ ያላቸው ናቸው።
 
ጥምረቱ እ.ኤ.አ በ2050 ከዓለም ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት 50 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።
 
በአፎምያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top