በአዲስ አበባ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ ተያዘ

2 Hrs Ago 21
በአዲስ አበባ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ ተያዘ

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ዝግታ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ አንድ ግለሰብ ልዩ ልዩ ማህተሞችና ቲተሮችን በመጠቀም ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ ተይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡    

ፖሊስ ተገቢውን የህግ ስርዓት ተከትሎ ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ በርካታ የተዘጋጁ እና ሊዘጋጁ የተሰናዱ ሀሰተኛ ሰነዶችን እንዲሁም ግለሰቡ ሀሰተኛ ሰነዶቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀምባቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችንም መያዙን ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪው ሀሰተኛ ሰነዶቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀምባቸው የመንግስትና የግል ተቋማት 51 ክብ፣ 73 የግርጌ ማህተሞች፣ አምስት ፕሪንተሮች፣ አንድ ኮምፒተር፣ አንድ  ላፕቶፕ  እንዲሁም በሃሰተኛ መንገድ የተዘጋጁ  የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል እንዲሁም የዲፕሎማ፣ የዲግሪ፣ የማስተርስ የትምህርት ማስረጃዎችን በተጨማሪነት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡

አዲስ አበባ ፖሊስ በሀሰተኛ ሰነድ አማካኝነት የሚፈፀሙ ልዩ ልዩ ወንጀሎችን በመከላከል ህገ-ወጦችን ተጠያቂ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡

በዚህ ተግባር ላይ ህብረተሰቡ ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያሳሰበው ፖሊስ፤ ተቋማት ለተለያዩ ጉዳዮች የሚቀርቡላቸውን ሰነዶች ትክክለኛነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top