ከዳግላስ DC-3 እስከ ኤርባስ A350-1000 ወጀቦችን የተሻገረ ጉዞ

16 Days Ago 461
ከዳግላስ DC-3 እስከ ኤርባስ A350-1000 ወጀቦችን የተሻገረ ጉዞ

ተቋም ትውልድን ተሻግሮ የሀገር ምልክት ሲሆን ምን ይመስላል ቢሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እና የፓንአፍሪካ ቀለም ነው፡፡ በአፍሪካ ግንባር ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ነው አየር መንገዱ፡፡ በደህንነቱ ብዙዎች የሚመርጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ማማ ላይ ለመውጣት እጅግ ከባድ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ ሊወዳደሩት ያልቻሉት ሊያወርዱት ብዙ ጊዜ ሞክረውት ያልሆነላቸው ጽኑ መሰረት ስላለው ነው፡፡

አየር መንገዱ የመጀመሪያ በረራውን ካደረገባት ዳግላስ DC-3 በአፍሪካ የመጀመሪያው እስከሆነው ኤርባስ A350-1000 የመጣበት መንገድ ሲፈተሸ ምን ይመስላል? እንዴትስ ፀንቶ ያለፉትን 78 ዓመታት በስኬት ጎዳና መጣ? ማዲባ ጥቁር አብራሪ አይተው የተደነቁበት እና ከራሳቸው ጋር የተሟገቱበት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በላቀ አገልግሎቱ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል። ከነዚህም መካከል ከስካይትራክስ ያገኘው የ"ምርጥ አየር መንገድ" ሽልማት፣ የዓለም የጉዞ ሽልማቶች እና በተደጋጋሚ የአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ በመባል ያገኛቸው ሽልማቶቹ ይጠቀሳሉ። አስተማማኝነቱ፣ ደኅንነቱ እና የላቀ የደንበኞች አገልግሎቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደም፣ በዓለም ደግሞ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል አስችለውታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታኅሳስ 12 ቀን 1938 ዓ.ም ተቋቁሞ መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም በአሥመራ በኩል አድርጎ ወደ ካይሮ የመጀመሪያውን በረራ አደረገ፡፡ የመጀመሪያውን በረራ የጀመረባት አውሮፕላን ደግሞ እስከ 28 ተሳፋሪዎች መያዝ የምትችለው ዳግላስ (Douglas C-47 Skytrain) ነች፡፡ አየር መንገዱ የተቋቋመው ከአሜሪካው ትራንስ ወርልድ አየር መንገድ ጋር በሽርክና ነው፡፡ የአሜሪካው አየር መንገድም አምስት ተጨማሪ C-47 አውሮፕላኖችን ገዝቶ ያቀረበ ሲሆን፣ የካይሮ በረራው በሳምንት አንዴ ቀጥሎ ወደ ጅቡቲ እና የመን እንዲሁም የሀገር ውስጥ በረራ ወደ ጅማ ተጀመሩ፡፡

በቀጣይ ዓመትም መዳረሻውን በማስፋት ወደ ናይሮቢ፣ ፖርት ሱዳን እና ቦምቤይ መብረር ጀመረ፡፡ በተመሳሳይ ዓመት ለሃጅ ወደ መካ ለሚጓዙት የቻርተር አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

አየር መንገዱ በ1950ዎቹ መዳረሻዎቹን ማስፋቱን የቀጠለ ሲሆን፣ እንደ ቦይንግ 720 ያሉ ትላልቅ አውሮፕላኖች ባለቤትም ሆኗል። ወደ ሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ በረራ በመጀመርም ዓለም አቀፍ አየር መንገድነቱን ያረጋገጠበት ሆኗል።

በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ ቦይንግ 727 እና 737 አውሮፕላኖችን በመግዛት ወደ ጄት ዘመን የገባ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የጉዞ መስመሮችንም በእጅጉ ማስፋት ችሏል፡፡ በመቀጠልም የቦይንግ 757 እና ቦይንግ 767 አውሮፕላኖችን በመጨመር አድማስ ማካለሉን ቀጠለበት።

ከ1983 እስከ 1987 ዓ.ም የነበረው ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የኢኮኖሚ ፈተናዎች የነበሩበት ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባው አየር መንገዱ ወጀቡን ተቋቁሞ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎቱን በቁርጠኝነት መስጠቱን ቀጠለ።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደ ቦይንግ 777 ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በአፍሪካ አስተዋውቋል። እነዚህ አውሮፕላኖች ነዳጅ ቆጣቢ እና የመንገደኞችን ምቾት ያሻሻሉ ነበሩ። ሕዳር 2004 የግዙፉ የአየር መንገዶች ጥምረት ስታር አሊያንስ አባል በመሆን በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ተዓማኒነቱን አጎናጽፏል።

አየር መንገዱ አገልግሎቱን ለማስፋት ባለው ቁርጠኝነትም በዘመናዊ አውሮፕላኖች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል። ተፈትሸው ብቃታቸው የተረጋገጡ አውሮፕላኖችን በመግዛትም ከግንባር ቀደሞቹ መካከል ነው፡፡ ሰኔ 2008 ዓ.ም በነዳጅ ቁጠባው የሚታወቀውን ዘመናዊ አውሮፕላን Airbus A350 XWB በለቤት የሆነ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ ሆኗል።

የአየር መንገዱን የአፍሪካ ቀዳሚነት የሚያረጋግጠው Airbus A350-1000

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት በአፍሪካ የመጀመሪያውን Airbus A350-1000 አውሮፕላን ተረክቧል፡፡ ይህም አየር መንገዱ በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት ያለውን ዕቅድ እና አቅም የሚያሳይ ነው፡፡ Airbus A350-1000 የተራቀቀ ኤሮዳይናሚክስ፣ ውስጣዊ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን፣ለመንገደኞች ምቹ አገልግሎት የመስጠት አቅሙን ይጨምርለታል። የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት አውሮፕላኑ በአየር መንገዱ ምድረ ቀደምት (Ethiopia land of origins) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

አየር መንገዱ ከDC-3 ወደ Airbus A350-1000 ያደረገው ጉዞ በአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍ የብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለው ነው። ዘርፉ ላይ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት በማድረግ፣ የደህንነት መስፈርቶችን በማሟላት እና ለደንበኞች እርካታ ቅድሚያ በመስጠት አፍሪካን ከዓለም ጋር በማገናኘት ላይ ይገኛል፡፡ በየጊዜው ከሚለዋወጠው የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር በመናበብ በዓለም አቀፍ አቪዬሽን ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ ከደመና በላይ መቅዘፉን ቀጥሏል።

አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል። ዕቅዱን ለማሳካትም በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚያስችለውን ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንበት እንቅስቃሴ ጀሟል፡፡ 124 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ያዘዘ ሲሆን፣ እነዚህ አውሮፕላኖች ሲጨመሩ መዳረሻዎቹ እና የአገልግሎቱ ጥራቱን የበለጠ የሚያሻሽሉለት ይሆናል፡፡ 

 

በለሚ ታደሰ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top