በየዓመቱ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቁ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ግንባር ቀደም ከሆኑት የጎዳና ውድድሮች መካከል አንዱ ነው። ሩጫው በ1994 ዓ.ም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ኩራት፣ የአትሌቶች መገኛ እና ንቁ ማኅበረሰብን መፍጠሪያ ተምሳሌት ሆኖ ቀጥሏል።
በሌሎች ዓለማት የሚያያቸውን መልካም ነገሮች ወደ ሀገሩ ለማምጣት የማይቦዝነው ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የታላቁ ሩጫን ሐሳብ ያመነጨው የዩናይትድ ኪንግደሙ "ኖርዝ ግሬት ራን" መነሻ በማድረግ ነው፡፡፡ ዓላማውም የብዙኃን ተሳትፎን በማበረታታት የኢትዮጵያን የሩጫ ባህል ለማሳደግ ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ሌሎች ድርጅቶች በርካታ ዕውቅናዎችን ያገኘ የጎዳና ላይ ውድድር ነው፡፡ ማኅበራዊ ለውጥ እንዲመጣ፣ ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እና አካባቢ ከብክለት እንዲጠበቅ ባለፉት 23 ዓመታት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የመጀመሪያው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በኅዳር ወር 1994 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲጀመር፣ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ 10 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን የመጀመሪያው የወንዶች የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊም አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ነበር፡፡
ታላቁ ሩጫ የሚለየው ታዋቂ አትሌቶችን፣ በቀጣይ በአትሌትክሱ ለመሳተፍ ተስፋ ያላቸውን ታዳጊዎችን እና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፉ ነው፡፡ በቅርቡ የህጻናት ውድድርን በማካተት ሁለገብ ተሳትፎን እውን ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህም ውድድሩ በፍጥነት እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ሲሆን የብዙ አትሌቶች መነሻም በመሆን የድርሻውን አበርክቷል፡፡
በጥቂት ዓመታት ውስጥም ከመላው ዓለም የመጡ ተሳታፊዎችን እና የአትሌቲክስ አድናቂዎችን ትኩረት በመሳብ ተሳታፊዎችን እና የድጋፍ ሰጪዎችን ቀልብ መያዝ የቻለም ሩጫ ነው፡፡ በዓመቱም የተሳታፊው ቁጥር እያደገ ሄዶ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሳተፍ ችሏል፡፡
ታላቁ ሩጫ ማኅበራዊ ግዴታን በመወጣትም ግንባር ቀደም ነው፡፡ ጤናማ አኗኗርን የሚያበረታታው ታላቁ ሩጫ፣ ከጤና ባሻገር በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይም ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ በየዓመቱ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመለየት እና መሪ ቃል በመንደፍ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን እና ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩት ውድድሮች እንደ ኤች.አይ.ቪ.ኤድስ፣ ሴቶችን ማብቃት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የመንገድ ደህንነትና የትራፊክ አደጋን መከላከል እና ሌሎች በርካታ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እየፈጠረ እና ድጋፍ እያደረገ የመጣ ሲሆን፣ በዘንድሮ 24ኛ ዓመቱም ''የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ህጻናት'' በሚል መሪ ቃል የተመጣጠነ ምግብ ለህጻናት አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዕድገት ባለው ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ በመረጣቸው ዘርፎች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ብቻም ሳይሆን ከሚሰበስበው ገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ፕሮጀክቶችን ሲያበረታታ ቆይቷል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቀረ ሳይሆን እንደ ባሕር ዳር እና ሐዋሳ ባሉ የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ውድድሮችን ያዘጋጃል።
በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ሺህዎችን በማሳተፍ ቀዳሚ የሆነው ታላቁ ሩጫ ፤ ከሩጫ ባሻገር ብዙዎች ተሰባስበው ባህላቸውን የሚያንጸባርቁበት እና በሙዚቃ የሚዝናኑበት መድረክም ሆኗል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አካባቢን የሚበክሉ ፕላስቲኮችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ባለመጠቀም ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል፡፡
ዓለም አቀፍ ታዋቂነቱ እየሰፋ የመጣው ታላቁ ሩጫ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የኮርፖሬቶች እንዲሁም ስፖንሰሮች ጨምሮ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ይሠራል።
ለበርካታ ባለተሰጥኦ ሯጮች ዕድልን እየፈጠረ ያለው ታላቁ ሩጫ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉበት መድረክ በመሆን ለሁሉም ዕድል የፈጠረ ነው።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያ የባለተሰጥኦ ሯጮች መፍለቂያ መሆኗን ከማሳየት አልፎ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቀ ያለ እና በጉጉት የሚጠበቅ ዓመታዊ የጎዳና ላይ ሩጫ ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘው ታላቁ ሩጫ የኢትዮጵያውያንን የላቀ ችሎታ እና የአንድነት መንፈስ እያጎለበተ ቀጥሏል።
ለሚ ታደሰ