የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ኤር ባስ A350-1000 በረራ ባደረገባቸው ከተሞች መገናኛ ብዙኀን ምን አሉ?

1 Day Ago 250
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ኤር ባስ A350-1000 በረራ ባደረገባቸው ከተሞች መገናኛ ብዙኀን ምን አሉ?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የግዙፉ A350-1000 ባለቤት የሆነ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ ነው። ይህም አየር መንገዱ በአፍሪካ አቪዬሽን ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዲይዝ አድርጎታል።

ኤር ባስ A350-1000 የመጀመሪያ መደበኛ በረራውን ወደ ናይጄሪያዋ ሌጎስ ነው ያደረገው፤ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ዱባይ፣ አክራ ጋና፣ ታንዛኒያ ኪሊማንጃሮ እና ዛንዚባር የተሳኩ በረራዎችን አድርጓል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው አፍሪካ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማሳደግ ረገድ ያለውን ከፍ ያለ ሚና አሳይቷል።

አዲሱ አውሮፕላን በረራ እንዲጀምርላቸው ዋሽንግተን ዲሲ፣ ለንደን፣ ፓሪስን እና ፍራንክፈርት ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል። ይህም ዓለም አቀፍ ፍላጎት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ተደራሽነቱን እና የላቀ አገልግሎቱን በማስፋት ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የላቀ አቅም ይሆነዋል፡፡

ይህ የአየር መንገዱ ስኬት እና የአፍሪካ ቀዳሚነት ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ከፍተኛ ሽፋን እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ በተለይም በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው A350-1000 መተዋወቁን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ለአፍሪካ አቪዬሽን ታላቅ ብሥራት እንደሆነ ነው መገናኛ ብዙኀኑ የገለጹት። አውሮፕላኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎቹ፣ በአነስተኛ የነዳጅ ፍጆታው፣ በውብ ውስጣዊ ክፍሎቹ እና በምቾቱ ልዩ መሆኑን ነው መገናኛ ብዙኀን የገለጹት።

አውሮፕላኑ የአፍሪካ የመጀመሪያውን በረራ ባደረገባት የናይጄሪያዋ ሌጎስ 257 የኢኮኖሚ እና 15 የቢዝነስ ክላስ በአጠቃላይ 272 መንገደኞችን አሳፍሮ ማርሻል ሙሐመድ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሱን የጠቀሰው "ቢዝነስ ዴይ" ይህ በአፍሪካ የመጀመርያውን ዘመናዊ አውሮፕላን መሆኑ ልዩ ክስተት እና ጉልህ ምዕራፍ እንደሆነ ዘግቧል።

"ኢንድፔንደንት" ሚዲያ ደግሞ አውሮፕላኑ በናይጄሪያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አቀባበል እንደተደረገለት ጠቅሶ፣ ተሳፋሪዎቹ በአውሮፕላኑ ምቾት፣ በመስተንግዶው፣ በሰፋፊ ስክሪኖቹ እና በፈጣን ገመድ አልባ ኢንተርኔት ምቹ ጉዞ እንዳደረጉ አስነብቧል፡፡

"አቪዬሽን ሚዲያ አፍሪካ" የተባለው የሀገሪቱ ሚዲያ በበኩሉ፤ የአውሮፕላኑ የመጀመሪያውን በረራ ወደ ናይጄሪያ ማድረግ በኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሆነ ዘግቧል፡፡

አውሮፕላኑ ኪሊማንጃሮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ "ዘ ሲትዝን ታንዛኒያ"፣ "ዴይሊ ኒውስ ታንዛኒያ" እና "አቪዬሽን ታንዛኒያ" ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ ሦስቱም ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው የአውሮፕላኑን ዘመናዊነት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚህ አውሮፕላን ባለቤት በመሆኑ በአቪዬሽኑ ዘርፍ ተወዳዳሪነቱ ከፍ እንደሚል እና ወደ ታንዛኒያ ያደረገው በረራ ምሥራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡

አውሮፕላኑ ከአፍሪካ ውጭ የመጀመሪያውን በረራውን ባደረገባት ዱባይም ሁነቱን አስመልክቶ ሰፊ ዘገባ ያቀረበው በጉዞ እና አቪዬሽን ላይ የሚጽፈው "ሳም ቹ" ሚዲያ  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የA350-1000 ባለቤት መሆን መዳረሻውን የሚያሰፋለት እንደሆነ ጠቅሶ ዘግቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን A350 ሞዴል አውሮፕላኖችን ቁጥር ወደ 21 የሚሳድግበት እንደሆነም ጠቅሷል፡፡ ወደ ዱባይ የጀመረው በረራው አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ለማስተሳሰር የላቀ ሚና እንዳለውም ይሄው ሚዲያ ዘግቧል።

አውሮፕላኑ 46 ምቹ "የቢዝነስ ክላስ" ተሳፋሪዎችን ጨምሮ እስከ 400 ሰዎችን መያዝ የሚችሉ መቀመጫዎች ያሉት መሆኑም ሌላው ልዩነቱ ሆኖታል፡፡ የቢዝነስ ክፍሉ ደግሞ ለተሳፋሪዎች እጅግ የሚመች እና ሰፊ መሆኑ ታዋቂ ሰዎችን በምቾት ለማጓጓዝ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የአየር መንገዱ ምቹ መስተንግዶም አውሮፕላኑ በብዙዎች ተመራጭ እንዲሆን የሚያስችለው ሌላው እሴት መሆኑን በረራ ያካሄደባቸው ሀገራት ሚዲያዎች ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጭ የዚህ አውሮፕላን ባለቤት የሆኑ አየር መንገዶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ አየር መንገዶች ውስጥም የኳታር አየር መንገድ፣ ብሪቲሽ አየር መንገድ፣ ቨርጅኒያ አትላንቲክ አየር መንገድ፣ ካታይ ፓስፊክ አየር መንገድ እና ጃፓን አየር መንገድ ይገኙባቸዋል፡፡

አየር መንገዱ በአጠቃላይ 21 "ኤር ባስ" አውሮፕላኖችን እየተጠቀመ ነው፡፡ በቀጣይም ሦስት ተጨማሪ A350-1000 አውሮፕላኖችን እንዲሁም 11 ተጨማሪ A350-900 አውሮፕላኖች ባለቤት ለመሆን ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡

ይህም በአውሮፓውያኑ 2035 በዓለም አቀፍ ደረጃ በአቪየሽኑ ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ አመራር እና የዘርፉን የላቀ ቴክኖሎጂ ታጥቆ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ያለውን ዕቅድ የሚያሳካበት ነው፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top