ኢትዮጵያውያን ለጥቁሮች ነፃነት የከፈሉትን ዋጋ ተከትሎ ጥቁር አንበሶች እየተባሉ ይጠራሉ።
ይህ የማንነታችን መገለጫች የሆነው ጥቁር አንበሳ መገኛው ደግሞ ከአዲስ አበባ በ570 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው የሀረና ጥብቅ ደን ውስጥ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ባሌ ዞን ሀረና ቡልቅ ወረዳ የሚገኘው የሀረና ጥብቅ ደን የአከባቢው እስትንፋስ ከመሆን ያለፈ የተፈጥሮ ሚዛን አስጠባቂም ነው ይባልለታል።
በዚህ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ከሚኖሩት የዱር አራዊት ውስጥ መጠርያችን እና መሞጋገሺያ ስማችን የሆነው ጥቁር አንበሳ ተጠቃሽ ነው።
የአከባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ይህንን ጥቁር አንበሳ ጠዋት እና ማምሻውን ከጎሬው ወጥቶ ተፈጥሮ በሰጠችው ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ሲገማሸር መመልከት ይቻላል።
የሀረና ጥቅጥቅ ደን የአከባቢ ስነ-ምህዳርን በመጠበቁ በካርቦን ሽያጭ ስርዓት ውስጥ ተካቶም ይገኛል።
አርሶአደር ከድር ጅብሪል የአከባቢው ነዋሪ ሲሆኑ አባቶቻችን ከደኑ እንጨት አይደለም ሀረግ አይቆርጡም ነበረ እኛም ያንን በማስቀጠል ደኑን እየጠበቅነው እንገኛለን ብለዋል።
ደኑ ለኛ ልባችን ነው የሚሉት አርሶአደር ከድር፤ በሀረና ወረዳ ውስጥ 16 ቀበሌዎች አሉ እያንዳንዱ ቀበሌ ካርታ አለው እስከ 10ሺ ሄክታር የሚሸፍኑ ቀበሌዎች አሉ በነሱ ውስጥም 7 ሰዎች ተመርጠው ደኑን ይጠብቃሉ ያስተባብራሉ ስለደኑ ያስተምሩናል ሲሉ ነው የገለፁት።
በካርቦን ንግድ ክፍያ ስርዓት ውስጥ በ2014 ዓ.ም የገባው የሀረና ደን በዛው ዓመት ብቻ 1.5 ሚሊየን ብር፤ በ2015 ዓ.ም ደግሞ 7 ሚሊየን ብር አስገኝቷል።
አርሶአደር ከድር እንደሚሉት በካርቦን ክፍያው በአከባቢው ወፍጮ ተተክሏል ቡና ወደ መካከለኛ ገበያ ለማቅረብ ተችሏል።
የሀረና ጥቅጥቅ ደን በተፈጥሮ ሀረግ ጥልፍ የተሸመነ የሚያስደምም መልክአ ምድር የተላበሰ ቦታ ሲሆን፤ በውስጡ አፈሩን ይዘው የማይሄዱ ኩልል ያሉ ብዙ ወራጅ ወንዞች ይገኙበታል።
የሀረና ጥብቅ ደን ወደ ካርቦን ሽያጭ ስርዓት የገባው ጥበቃው የተስተካከለ እና ሰፊ መሬት በመያዝ ለአካባቢ አየር ጥበቃ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል የሀረና ቡልቅ ወረዳ አከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ መሀመድ ከድር።
ለአርሶአደሮቹ ክፍያው ደርሶ ለልማት እንዲውል የሚያደርግ ማህበር ተቋቁሞ በስራ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ኃላፊው፤ ገንዘቡም ደኑን ለመጠበቅ ለአከባቢው ልማትና ለችግኝ ጣቢያ ይውላል ሲሉ ጠቁመዋል።
የሀረና ጥቅጥቅ ደን የምድር ሳንባ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ያደጉ ሀገራት ከተለያዩ ፋብሪካዎቻቸው በሚያወጡት በካይ ጋዝ አለም የአየር ንብረቷ ሲጎዳ በቀጥታ የገፈቱ ቀማሽ የሚሆኑት ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው።
አሁን ላይ ከሞላ ጎደል በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የተፈጥሮን ሚዛን ጠባቂ ለሆኑ ጥቅጥቅ ደኖች የካርቦን ክፍያ ስርዓት ተዘርግቶ ይገኛል።
አሁንም ግን ምድርን በሚዛን እያሻገሩ የሚገኙት እንደሀረና ያሉ ጥቅጥቅ ደኖች ናቸውና ነገ የተሻለ የአየር ንብረት እንዲኖር ምርታማነትን ለመጨመር አካባቢን ለመጠበቅ ችግኞችን መትከል አግባብ ነው።
በናርዶስ አዳነ